ዓባይና የአሜሪካ ጨዋታ

መስፍን ወልደ ማርያም
ሰኔ 2005
በአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ-ዓመት አስተሳሰብ ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሰው ዓላማ ለአውሮፓ ቄሣራውያን ዋና ግባቸው ሆኖ እስከሃያኛው ምዕተ-ዓመት ዘልቆአል፤ አሀን ፈጽሞ በተለየ ዘመን አሜሪካ ይህንን አስተሳሰብ ይዞ የተነሣ ይመስላል።
ኢትዮጵያን የተቆጣጠረ ዓባይን ይቆጣጠራል፤ ዓባይን የተቆጣጠረ ግብጽን ይቆጣጠራል፤ ግብጽን የተቆጣጠረ ኃይል ቀይ ባሕርን ከመግቢያና መውጫው ጋር ይቆጣጠራል፤ ቀይ ባሕርን ከመግቢያና መውጫው ጋር የተቆጣጠረ ኃይል ዓለምን ይቆጣጠራል።
አሜሪካ በግብጽ ላይ የተከለው ጥፍሩ ሲነቃነቅ መነቀሉ አለመቅረቱን ስላወቀው ሌላ የሚተክልበት አገር ይፈልጋል፤ በአካባቢው የግብጽን ነፍስ የሚነካ ከኢትዮጵያ የተሻለ አገር የለም፤ ለአሜሪካ ዓለም-አቀፍ ዓላማ ኢትዮጵያ ስትመረጥ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም፤ በመሀከለኛው ምሥራቅ የአረቦችን የተባበረ ኃይል ለመቋቋም የተመረጡ ሦስት አረብ ያልሆኑ አገሮች — ቱርክ፣ ኢትዮጵያና ፋርስ (ኢራን) — ነበሩ፤ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካ ዓለም-አቀፍ ኃይል መሰማት በጀመረበት ጊዜ ኢትዮጵያን ከከበቡአት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ጋር የነበርዋትን የቆዩ ውዝግቦች ለመቋቋም የአሜሪካ ድጋፍ በጣም አስፈላጊ ነበር፤ አሜሪካን ከአውሮፓ አገሮች ጋር እየመዘኑና እያመዛዘኑ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር የተደረገው ዲፕሎማሲ (ዓለም-አቀፍ የሰላም ትግል) የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት በእውነት ከሚያኮሩት ተግባሮች አንዱ ነው፤ ይህንን ትግል አምባሳደር ዘውዴ ረታ ምስጋና ይድረሰውና የኤርትራ ጉዳይ በሚለው መጽሐፉ ግሩም አድርጎ አሳይቶናል።
ምናልባት ገና ያልተጠና ጉዳይ በዘመኑ ኢትዮጵያ የነበራት ታሪካዊ ክብር ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታሪክና ዝና ጋር ተዳምሮ በአፍሪካ ተደማጭነት ነበራት፤ ይህንን ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገሮች ላይ የነበራትን ጫና (የዛሬውን አያርገውና) በመጠቀም አሜሪካ አፍሪካን በሙሉ ለዓላማዋ ለማሰለፍ ኢትዮጵያን መሣሪያዋ ለማድረግ ትሞክር ነበር።
እየቆየ የኢትዮጵያ መንግሥት የነጻነት መንፈስን በማሳየት ለአሽከርነት አልመች በማለቱና ለአሜሪካም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች (የእውቀት ጥበቦች) በመፈጠራቸው ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ዓለም-አቀፍ ዓላማ አስፈላጊነትዋ በመቀነሱ አሜሪካ ኢትዮጵያን ችላ ማለት ጀመረ፤ የ1966 ግርግር ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን ጠለቅ ብሎ ማጥናት ያስፈልጋል፤ በዚህ መሀልም የሶቭየት ኅብረት ዓለም-አቀፋዊ ጉልበት እየተሰማ በመሄዱ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ዓላማ ቀስ በቀስ እየለወጠ ሄደ፤ ከዚህም ጋር የሶቭየት ኅብረት ተጽእኖ እያደገ ሄደ፤ የአሜሪካ አያያዝ እየላላ ሲሄድ የሶቭየት ኅብረት አያያዝ እየጠበቀ ሄደ፤ 1966 የአሜሪካ መውጫና የሶቭየት መግቢያ ሆነ ለማለት ይቻል ይሆናል፤ ከዚሁ ጋር አብሮ የሚታየው በኢትዮጵያ የባህላዊው ሥርዓት መሰነጣጠቅና የቆየው ትውልድ መዳከም ነው፤ የአሜሪካ መዳከም ሶቭየት ኅብረትን ሲያጠነክር፣ የአሮጌው ትውልድ መዳከም አዲሱን ትውልድ አጠነከረ፤ ይህ ማለት አሮጌው ትውልድ ከአሜሪካ ጋር የተያያዘውን ያህል አዲሱ ትውልድ ከሶቭየት ኅብረት ጋር ተያያዘ፤ የኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታ ብቻውን ለውጥ እንዳላመጣና ዓለም-አቀፍ ሁኔታዎችና የልዕለ ኃያላኑ ተጽእኖም ምን ያህል እንደነበረ አመላካች ነው።