የዓባይ ጉዳይ እኛ ዜጎችም ያገባናል።
የዓባይ ጉዳይ እኛ ዜጎችም ያገባናል።
It is so!!!

ግብፅና ኢትዮዽያ በዓባይ ግድብ ጉዳይ የቃላት ጦርነት ከከፈቱ ሰንብተዋል። ዓባይ ወንዝ ታሪካዊ ከመሆኑ
የተነሳ የሁለቱም ሀገሮች እሰጣገባም ታሪካዊ መንስኤ አለው። ኢትዮዽያ የዓባይ ወንዝ አቅጣጫ መቀየሯ በተሰማ ማግስት
የግብፅ ፖለቲከኞች (አንድም ተደናግጠዋል አልያም የህዝብ ስሜት ለማስቀየር ፈልገዋል) አላስፈላጊ የማስፈራርያ
ቃላት መሰንዘር ጀመሩ። የኢትዮዽያ የትእግስት መልስ ወደነዋል።
የዓባይ ጉዳይ በባህሪው ለደረቅ ጦርነት የሚጋብዝ ባለመሆኑ ችግሩ ለመፍታት ያለው ብቸኛ አማራጭ
‘ድርድር’ መሆኑ ግልፅ ነው። ግብፆች ይህንን የድርድር መንገድ አሁን አሁን የገባቸው ይመስላል ወይም ሊገባቸው
ይገባል። ድርድሩ ለመጀመር ይመስላል የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አዲስ አበባ ድረስ መጥቶ ከኢትዮዽያዊው አቻው
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር ሲነጋገር ቆየ። በአንደኛ ሁለተኛ ዙር ውይይታቸው ያለ ስምምነት ተበተነ። መግለጫ
ለመስጠት ታቅዶ የነበረው ክፍለ ግዜ ተሰረዘ። እኛም አልደነቀንም። በሦስተኛው ዙር (ይመስለኛል) በወሳኝ ጉዳዮች
(ፖለቲካና ቴክኒክ) መስማማታቸው አስረዱን።
ዶ/ር ቴድሮስ ከግብፃዊ አቻው ጋር ‘ዉጤታማ ውይይት’ ማድረጉ በትዊተር (Twitter) ገፁ አስነበበን።
ጥርጣሬን ገለፅኩ። ምክንያቱም እንዴት ዉጤታማ ውይይት ሊያደርጉ ይችላሉ? እንዴት በዓባይ ጉዳይ በአጪር ግዜ ሊስማሙ
ይችላሉ? እነኚህ ጥያቄዎች መነሳት ያለባቸው ግብፅና ኢትዮዽያ በዓባይ ጉዳይ ሲያራምዱት የነበረ ብሄራዊ አቋም
የማይገኝ ከመሆኑ አንፃር ሲታይ ነው።
ግብፅ ጉዳዩ ለመፍታት ያስቀመጠቻቸው የድርድር ነጥቦች አሉ፥ (1) ድርድሩ እስኪካሄድና መፍትሔ እስኪገኝ
ድረስ የግድቡ ግንባታ ‘መቆም’ እንዳለበት፣ (2) የግድቡ መጠን ከ74 ቢልዮን ኲቢክ ሜትር ወደ 14 ቢልዮን
ኲቢክ ሜትር ዝቅ ማለት እንዳለበት (ይህንን ቅድምያ የሚሰጡት ነው)፣ ከዛ በኋላም (3) የግድቡ ዲዛይን በግብፅ
ባለሞያዎች መፈተሽ እንዳለበት … ወዘተ ያስቀምጣሉ።
እስካሁን በሚድያ እንደሰማነው የኢትዮዽያ መንግስት አቋም ደግሞ (1) የግድቡ ግንባታ እንደማይቆም፣ (2)
ግድቡ ወደ ግብፅ የሚሄደው የውሃ መጠን እንደማይቀንስ (ይሄ እንኳ አቋም አይደለም ማብራርያ እንጂ) (3) ኢትዮዽያ
የድሮ የውሃ አጠቃቀም ውል እንደማትቀበልና የዓባይ ዉሃ ለኤለክትሪክ ሃይል ማመንጫ የመጠቀም መብት እንዳላት ወዘተ
…።
በተጨማሪም ግብፅ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም (የውሃ ደህንነት) ለማስከበር ‘ማንኛውም ዓይነት መንገድ’
(የሃይል እርምጃ ወይ ጦርነት ጭምር መሆኑ ነው) እንደምትጠቀም ስታስታውቅ ኢትዮዽያ ግን ጉዳዩ በሰለማዊ መንገድ
ወይ በድርድር መፈታት እንዳለበት ትገልፃለች። እንዲህ የሚጣረሱ (የማይገናኙ) አቋሞች ይዘው እንዴት በሁለት ቀናት
ውይይት ሊስማሙ ይችላሉ? የገረመኝ ጥያቄ ነበር።
በዚህ ጉዳይ በትክክል መስማማት የሚቻለው አንዱን ወገን ወይ ሁለቱም ወገኖች ብሄራዊ ጥቅማቸውን አሳልፈው
መስጠት ከቻሉ ብቻ ነው። ለመሆኑ የተስማሙበት ነጥብ ምንድነው? እንደ ኢቲቪ ዘገባ ከሆነ “… ቀደም ብሎ በነበረው
ስምምነት መሰረት አለም አቀፉ የባለሙያዎች ፓናል ባቀረባቸው የወደፊት ሀሳቦች ላይ ሱዳንን በመጨመር የሶስትዮሽ
ምክክር ለመቀጠል ተስማምተዋል” ይላል። ትንሽ ወረድ ብሎ ደግሞ “… አለም አቀፍ የባለሙያዎች ፓናልን በተመለከተ
ባስቀመጥነው አሰራር መሰረት የአጥኝ ቡድኑ ያወጣቸውን የወደፊት ሀሳቦች ለመተግበር ተስማምተዋል፡፡” የሚል
እናገኛለን።
ስምምነታቸው ይህ ከሆነ ‘በትክክልም ተስማምተዋል’ ባይ ነኝ። ቀደም ሲል ‘በዓባይ ጉዳይ በቀላሉ
መስማማት የሚቻለው ቢያንስ አንደኛው ወገን ብሄራዊ ጥቅሙ አሳልፎ ሲሰጥ ብቻ ነው’ የሚል መልእክት ያለው ሓሳብ
አስፍሬ ነበር። ጉዳዩ አሁን ተፈቷል። ስምምነቱ ተግባራዊ ከሆነ የኢትዮዽያ መንግስት ተሸንፏል ማለት ነው። ዶ/ር
ቴድሮስ አድሃኖም በትክክል ተሸውዷል።
የኢትዮዽያ መንግስት የዓባይ ግድብ ለፖለቲካ ፍጆታ ከማዋል ውጪ (‘ያልተደፈረ ደፍረናል፣ ልማት ለማምጣት ጥረት
እያረግን ነን …’ ከሚል ፕሮፓጋንዳ በዘለለ) በትክክል ግድቡ በጥቅም ላይ ለማዋል ተነሳሽነት ያንሰዋል ወይ
እንዴት መጠቀም እንደሚችል የሚያሳይ ትክክለኛ ስትራተጂና ግልፅ አቅጣጫ የለውም። መንግስት ጉዳዩ በድርድር መፈታት
እንዳለበት ያውጃል። ግን ድርድር ምንድነው? ምን ምን ያጠቃልላል? ለድርድር የሚቀመጡ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
(መለየት አለባቸው)። የሚደራደሩ ብቁ ባለሙያዎችና ፖለቲከኞች አሉን ወይ? የድርድር ነጥቦቹ በበቂ ጥናት የተደገፉ
ናቸው ወይ? በድርድሩ ወቅት compromise የሚደረጉና የማይደረጉ interests በትክክል ተቀምጧል ወይ?
Compromise የሚደረጉ ነጥቦች ብሄራዊ ጥቅማችን (National Interest) እንደማይጎዱ ተጠንቷል ወይ?
ድርድሩ ውጤታማ ባይሆንስ ቀጣዩ ሂደት ወይ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማስቀመጥ ተሞክሯል ወይ (ሀገር በማይጎዳ
መልኩ እንዲከወን ለማድረግ)? ባጭሩ ሁሉም የምናደርገው ነገር ጥናት መሰረት ያደረገ ነው ወይ? ጥናት የሚያካሂዱ
በቂ ተቋማት አሉን ወይ? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች አርኪ መልስ ማግኘት አለባቸው። ‘በድርድር መፍታት አለብን’
የሚል አቋም ስለያዝን ብቻ ‘ተደራድረን እናሸንፋለን’ ማለት አይደለም።
በዓባይ ጉዳይ ሀገራችን ያላት አዎንታዊ ጎን ስሜታዊነት (‘ሀገር ወዳድነት’ ልበለው)ና የዓለም አቀፍ
ዲፕሎማቲክ ድጋፎች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ደግሞ ለሀገር ትንሽ ቢያበረክቱ በጦርነት ወቅት ብቻ ነው።
በቴክኒካዊ ድርድር ዋጋ የላቸውም። በጦርነት የተራቀቁ የጦር መሳሪያዎችና አርበኝነት ዋነኘቹ ሊሆኑ ይችላሉ።
በድርድር ግን የዘርፉ ባለሙያዎችና የጠለቀ የፖለቲካ እውቀት አስፈላጊ ነው።
አሁን የሁለቱም ሀገሮች የቴክኒክ ባለሙያዎች ዓቅምና ልምድ ስናወዳድራቸው ሰማይና መሬት ሁኖው እናገኛቸዋለን።
ሩቅ ሳንሄድ በግብፅ በዓባይ ጉዳይ ጥናት ያካሄዱና ብዙ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎችና ተቋማት መዓት ናቸው።
በኢትዮዽያ አንድም ተቋም የለም። በግብፅ ብዙ ባለሙያዎች የፖለቲከኞች አማካሪዎች ናቸው። የኢትዮዽያ መንግስት
ባለሙያዎች አያስተናግድም። በግብፅ ማንኛውም ፖሊሲ ጥናት መሰረት ያድረገ ነው። በኢትዮዽያ ሁሉም ነገር በደመ ነፍስ
ነው።
ኢትዮዽያ ብቁ የቴክኒክና የፖለቲካ ተደራዳሪዎች የሏትም። በኢትዮ-ኤርትራ የዶብ ጉዳይ ሀገራችን በጦርነት
አሸንፋ ወደ ድርድር ተመለሰች፤ ከጦርነት በኋላ ወደ ድርድር መመለስ በራሱ የፖለቲካ እውቀት ማነስ ውጤት ነው።
በድርድሩ ተሸነፈች፤ ምክንያቱም የኢትዮዽያ ተደራዳሪዎች ብቁ አልነበሩም። ብዙ ግዜ ኢትዮዽያ በጦርነት እንጂ
በድርድር አታሸንፍም (ከግብፅ ጋር ጦርነት ያስፈልጋል ግን አላልኩም)።
አሁም ሁለቱም ሀገሮች የተስማሙበት የቴክኒክና የፖለቲካ ድርድር ለግብፅ ትልቅ ድል ነው። ምክንያቱም
(1) የስምምነቱ ነጥብ እንደሚለው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድኑ የሚያወጣቸው የወደፊት ሓሳቦች ለመተግበር
ተስማምተዋል። መጀመርያ እነኚህ ዓለመቀፍ አጥኚ ባለሙያዎች እነማን ናቸው? በቁጥር አስር ሲሆኑ ሁለት ግብፃውያን፣
ሁለት ሱዳናውያን፣ ሁለት ኢትዮዽያውያንና የተቀሩት አራት ከሌሎች ሀገሮች ይመረጣሉ። የኢትዮዽያና የግብፅ ባለሙያዎች
(በዓባይ ጉዳይ ማለቴ ነው) በዓቅምና ልምድ ይመጣጠናሉ? ግብፅ በሌሎቹ (የሱዳን ጨምሮ) የቡድኑ አባላት ተፅዕኖ
መፍጠር እንደማትችል ማረጋገጫ አለን? ወይ በምንና እንዴት እንደምናመጣጥነው ተዘጋጅተናል? አጥኚ ቡድኑ እንዴት ነው
ዉሳኔ የሚያስተላልፈው? ግልፅ የሆነ መረጃ አለ? (እርግጥ ነው ‘ወደፊት እናየዋለን’ ትሉናላቹ)።
(2) እንበልና ‘አለማቀፉ አጥኚ ቡድን’ ግድቡ ወደ ግብፅ የሚሄደው የውሃ መጠን እንደሚቀንሰው
ቢያረጋግጥ የኢትዮዽያ መንግስት ግድቡ ለማቆም ይገደዳል ማለት ነው? ይሄን ሁሉ ኢንቨስት የተደረገው ሃብትና ጉልበት
ከንቱ ሊቀር ነው? ኢትዮዽያ አቋሟን እንደገና መፈተሽ አለባት።
ባለፈው በተደረገ ድርድር ግብፃውያን ሸውደውናል ማለት ይቻላል። አሁን የኢትዮዽያ መንግስት ማድረግ ያለበት
ሁሉንም ኢትዮዽያውያን ባለሙያዎች እንዲሳተፉ መጋበዝ፣ ወቅታዊ መረጃዎች በግዜውና በአግባቡ ለህዝብ መስጠት፣ ግድቡ
ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ብቻ አለማዋል ፤ የሀገር ጉዳይ ነውና፣ የሁሉም ዜጎች ደህንነት ያለ አድልዎ ይጠብቅ፤ ሀገር
የሚጠብቁና የሚገነቡ ዜጎች ናቸውና።
የዓባይ ጉዳይ እኛ ዜጎችም ያገባናል።
It is so!!!
No comments:
Post a Comment