አባሎቻችንና አመራሮቻችን ላይ እየተወሰደ ያለውን ህገ-ወጥ እስርና ድብደባ በህዝባዊ ንቅናቄ እንታገለዋለን፣ እናስቆመዋለን!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
ፓርቲያችን አንድነት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገባቸውን ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነት እንዲጎናፀፉ በማለም በፅናት ትግሉን ቀጥሏል፡፡ በዚህ ሂደትም ቁርጠኛ አመራሩና አባላቱ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ አሁንም እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡በተለይም የፓርቲያችንን መዋቅር ለማፍረስ እረፍት የሌለው ገዥ ፓርቲ በክልሎች የሚገኙ አመራሮቻችንን ማሰር፣ መደብደብ፣ ማግለልና ስም እየለጠፉ ማስፈራራት ዋና ተግባሩ አድርጎ እየሰራበት ነው፡፡ አባሎቻችንና አመራሮቻችንም ሳይበገሩ በቁርጠኝነት ትግሉን በሰላማዊ መንገድ በመግፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰላማዊ ትግል የሚያስከፍለው ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ቁርጠኝነቱም አላቸው፡፡
በየጊዜው በአባሎቻችንና አመራሮቻችን ላይ እየተወሰደ ያለው ህገ-ወጥ የሰብዓዊ መብት ገፈፋ፣ ጭካኔ የተሞላበት ግርፊያና ድብደባ እንኳን መንግስት ነኝ ከሚል አካል ቀርቶ ከጨካኝ ወንበዴ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ይህንን ድርጊት ከመቃወም በዘለለ የህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ማስቆም እንደሚገባ አጠንክረን እናምናለን፡፡ ህዝብ ላይ የሚፈፀም ግፍና በደል ሊፈታና ሊወገድ የሚችለው ግፍና በደል ባንገፈገፈው ህዝብ ተከታታይና ትርጉም ያለው ትግል ነው፡፡
በፓርቲያችን አመራሮች ከሚፈፀሙ ህገ-ወጥ የገዥው ፓርቲ ግፎች አንዱ አቶ ተገኝ ሲሳይ በተባለ የምእራብ አርማጭሆ የአንድነት ሰብሳቢ ላይ የተፈፀመው ህገ-ወጥ እስርና በታሰረበት የተፈፀመበት ከፍተኛ ድብደባ ነው፡፡ አቶ ተገኝ ሲሳይ ክስ ሳይመሰረትበት የአደራ እስረኛ ነው በሚል ከመጋቢት 17 ቀን 2005ዓ.ም ጀምሮ አፍነው በመውሰድ፤ እጁ እስከሚሰበር በመደብደብና ህክምና እንዳያገኝ በማድረጋቸው በህይወት መቆየቱ አጠያያቂ እስከሚሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
በአዲስ አበባም የወረዳ 19 ምክትል ሰብሳቢ የሆነው ወጣት ባህሩ ራህመቶ ከቤቱ ታፍኖ ተወስዶ የት እንደገባ ሳይታወቅ ከቆየ በኋላ ማዕከላዊ ይገኛል፡፡ ፓርቲያችን አመራሮችና አባላት ላይ እየተፈፀመ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት፣ ህገ-ወጥ እስርና ድብደባ ከማውገዝም ባሻገር ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን ትግሉን እንቀጥላለን፡፡ በህዝባዊ ንቅናቄ አፈናና እስሩን እንታገላለን፡፡ ይህንንም በቅርቡ ይፋ የምናደርግ ይሆናል፡፡
ምንም ዓይነት ርምጃ ከትግል መስመራችን ፈቀቅ አያደርገንም!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment