የማለዳ ወግ … ስደተኛው ዘፋኝ በሳውዲ በርሃ …(ከጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ)
December 16, 2013የእንጀራ ነገር ሆኖብኝ እጓዛለሁ ፣ እጓዛለሁ ፣ እጓዛለሁ … እንደጨው ተበትነናልና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወገኖቸን በየሔድኩበት ከተማ ፣ እግር በጣለኝ የሳውዲ የቀለጡ በርሃዎች ወንድም እህቶቸን አገኛለሁ ። ላፍታም ቢሆን ጊዜ ሰጥቸ እየኑሩት ስላለው ኑሮ ፣ እየገፉት ስላለው ክፉም ደግ ተሞክሮ እጠይቃቸዋለሁ አንድም ሳይደብቁ የሆድ የሆዳቸውን ያጫውቱኛል …እለተ ቅዳሜ በማለዳው ያቀናሁት በያንቦና በጅዳ መካከል በምትገኝ የዋዲ በርሃ ዙሪያ ነበር ። አየሩ ተቀያይሯል ፣ ከዚህ ቀደም ወደዚህ ቦታ ሳመራ እንደ እሳት ነበልባል የሚጋረፈው ሙቀት ዛሬ የለም ። ለስራ ወዳቀናሁበት በድቅድቁ በርሃ ላይ በተሰራው የድንጋይ መከስከሻ ፋብሪካ እንደደረስኩ አንድ መልከ መልካም ወንድም የግቢውን በር ከፍቶልኝ ለመግባት ወዴት መሄድ እንደምፈልግ የጠየቀኝ ወጣት ሃበሻ ለመሆኑ ቅንጣት ያህል አልተጠራጠርኩምና የሚጠይቀኝን ትቸ እኔው ጠየቅኩት “ሃበሻ ነህ! ” ነበር ያልኩ ። ይህን ስጠይቀው እንደ መሽኮርመም እና እንደመሳቅ እያለ “አዎ ሃበሻ ነኝ ፣ ኢትዮጵያዊ! ” ሲል መለሰልኝ! ብዙ ሃበሾች አላችሁ? ስል ጥያቄየን ቀጠልኩ “አዎ አምስት ሃበሾች አለን! ” አለኝ ፈገግ እያለ … በአሻጋሪ መምጣቴን የሚጠብቅ የፋብሪካው ሃላፊ “አስገባው ፣ አስገባው! ” ሲል ፍልቅልቁ ወንድም ተደናግጦ በወራጅ ብረት እንደነገሩ የተዘጋውን የግቢ ብረት አጥር ከፍቶልን እኔና የስራ ባልደረባ ረዳቴ የፊሊፒን ዜጋው ግላዲ ወደ ግቢው ስንገባ በመስኮት በኩል አንገቴን ወጣ አድርጌ ስራየን ከዋውኘ እንደማገኘው ቃል ገብቸለት ወደ ውስጥ ገባሁ …

ሱዳኑ የፋብሪካ ሃላፊ ከድንጋዩ መፍጫ የቅርብ ርቀት ካለው ጋራጅ አጠገብ ከተሰራች ባለሁለትና ሶስት ዛኒጋባ ቆርቆሮ ቤት ወጥቶ ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጥቶ ተቀበለን ። ድንጋዩን እየከሰከሰ ጠጠር የሚያደርገው ፋብሪካ ነጭ አመድ ወደ ሰማይ እየተፋ የጓራል …ዲንጋው እየተፈጨ ጠጠር እየተሰራ መሆኑ ነው! የመንገድ መደልደያ ፣ የምንገድ መጥረጊያ እና የመንገድ ማለስለሻ ዳምጤ ከባባድ የኮንስትራክሽን መኪኖችን ጨምሮ ጥገና የሚያስፈልጋቸው መኪኖች ጋራጁን አጨናንቀውታል … ከጋራጁ ጀርባ ደግሞ እኛ መመርመር ያከብን የተሽከርካሪ ጎማ መአት ተከምሯል። …አምስት የተባሉትን ሃበሾች አግኝቸ እስካዎጋቸው ቋምጫለሁ …የፊት የፊቱን እያስቀረብኩ ለፊሊፒኑ አጋሬ ምን መስራት እንዳለበት በማሳወቅ ስራውን አጣድፊ ግን በአግባቡ መርምሬ እንደጨረስኩት ሌሎች ሁለት ሃበሾች ሃበሻ ወንድማቸው መምጣቴን ሰምተው ኖሮ በፈገግታ እየተፍለቀለቁ መጥተው ሰላምታ ተለዋዎጥን …
ሃበሻ ዝር በማይልበት በርሃ ያገኙኝን ወንድም እነርሱም ሊያስተናግዱ ሊያጫውቱኝ እንደቋመጡ አልጠፋኝም … በተንቀሳቃሽ ኮንቴነር በፋይዚት ግሩም ሆና የተሰራቸው ማረፊያ ቤት ከጋራጁ የቅርብ ርቀር ትገኛለች ። አቧራ የጎረሰውን እጀን ሳልተጠብ በበርሃው ወዳገኘኋቸው ወንድሞች ማረፊያ ቤት አመራሁ … ረመድ ረመድ እያልኩ ከመድረሴ ወንድሞቸ በደስታ እየተፍለቀለቁ ግማሽ መንገድ ላይ ተቀበሉኝ ! ጠባቧ ቤት ማረፊያ ቤት ብቻ እንዳልሆነች ከበር የተደረደሩትን ጫማዎች ስመለከት ገባኝና ጫማየን አውልቄ “ቤት ለእንቦሳ! ” ብየ ዘው ብየ ገባሁ… ቤቷ ጽድት ያለች ናት … ሶስት አልጋዎች በሶስቱ የቤቱ ማዕዘኖች ጥግ ይዘው ተዘርግተዋል ። የተቀበሉኝ ወንድሞቸ ሶስት ሲሆኑ ዘግየት ብሎ ሌላ ወንድም ገባ … አምስተኛው ወንድም የት እንዳለ ስጠይቅ እሱ ስራ ላይ እንደሆነ ገለጹልኝ። ሁላችንም የምናወራው ከአልጋዎች ላይ ተቀምጠን ነው ። እንደገባኝ ከሆነ አልጋዎች ይተኛባቸዋል ብቻ ሳይሆን በመቀመጫነት ያገለግላሉ! … ጫዎታችን ከመጀመራችን በፊት እጀን ለመታጠብ ውሃ ቢጤ ስጠይቅ ድምጹ ጎርነን ያለው “ሸዋንግዛው እባላለሁ!” ብሎ የተዋወቀኝ ወንድም በእጅ ከምትያዝ ማቀዝቀዣ ውሃ ይዞ ወደ ” በር ላይ ላስታጥብህ! ” ብሎ ግማሽ ጎኔን ከበሩበወጣ አድርጌ እንደነገሩ ጣቶችን ውሃ አስነካሁ ብል ይሻላል ፣ ብቻ ታጠብኩ ።