በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ኢንቨስተር መንግስት ነው ሲል የአለም ባንክ አስታወቀ
እንደ ሪፖርተረ ዘገባ፤ የባንኩ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጉዋንግ ቼንግና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር አብርሃ ተከሰተ በተገኙበት በሸራተን አዲስ ይፋ የተደረገው የዚህ ሪፖርት ዋነኛ ትኩረት መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ሚና የሚመለከት ነው።
ሪፖርቱ፤ በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ እየጨመረ የመጣው የመንግሥት ኢንቨስትመንትን በጥልቀት የመረመረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ኢንቨስትመንት ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ሁለት ሦስተኛ የሚሆነውን ድርሻ የሚወክል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በጣም በሰፊው ኢንቨስት እያደረጉ ከሚገኙ መንግሥታት ተርታ ተመድባለች፡፡
እንደ ሪፖርቱ በኢንቨስትመንት ረገድ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚበልጡት ሁለት አገሮች፦ ተርክሜኒስታንና ኢኳቶሪያል ጊኒ ናቸው።
ይህ የመንግስት ድርሻ የግል ዘርፉን ያለ ቅጥ በማቀጨጭ የመጣ መሆኑንም የባንኩ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በሪፖርቱ እንደተመለከተው በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንቨስትመንት ምጣኔው ከመጨረሻ ወደ ላይ ስደስተኛ ደረጃን ነው የያዘው፡፡
የመንግሥት ዘርፍ ኢንቨስትመንት- ከግሉ ዘርፍ ጋር ሲነፃፀር ሦስት እጥፍ መሆን መቻሉ፤ ሌላው በአትኩሮት የተነገረ ጉዳይ እንደነበር ከሪፖርተር ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።
የዓለም ባንክ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው የ10.7 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ከቀጠለ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ለመሠለፍ ከአሥር ዓመት በላይ ላይፈጅባት እንደሚችልም መዘገቡ ተመልክቷል።
አይኤም ኤፍም በቅርቡ መንግስት የግሉን ዘርፍ እንዲያጠናክር ማሳሰቡ ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም ባንክ ለቀረበው አስተያየት የሰጠው መልስ በዘገባው አልተገለጸም።
የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያውያን ለመብታቸው መከበር የሚያሰሙትን ድምጽ ይሰማል ሲሉ ወ/ሮ አና ጎሜዝ ተናገ
ኢሳት ዜና:- የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል የሆኑት እና በምርጫ 97 ወቅት የህብረቱ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የነበሩት ወ/ሮ አና ማርያ ጎሜዝ ይህን የተናገሩት ኢትዮጵያውያን ዛሬ በአውሮፓ ህብረት መቀመጫ ፊትለፊት ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ነው ። ወ/ሮ አና ጎሜዝ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያውንን ጩሀት ሰምቶ መልስ እንደሚሰጥ ተናግረው፣ በግላቸው ከኢትዮጵያውያን ጎን ቆመው ለውጥ እስከሚመጣ እንደሚታገሉ ተናግረዋል።በተቃውሞው ላይ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ውስጥ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዘርዝረው ለአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት አቅርበዋል።
ከተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ሻውል ሰልፉ የተሳካ እንደነበር ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ከ493 ሺ በላይ ሄክታር መሬት ደን እየወደመነ ተባለ፣ ክልሉ ግን አስተባብሎአል።
ኢሳት ዜና:- በደብረ ማርቆስ የየራባ ደን ፤በአዊ ዞን እንጅባራ የገንብሃ ጫካ ፤በደብረ ታቦር እና በኮምቦልቻም አመታትን ያስቆጠሩ ደኖች እየጠመነጠሩ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል፡፡ከፍተኛ የደን ቆረጣ በሚካሄድባቸው በአዊ እና በደብረማርቆስ አካባቢዎች ነዋሪዎች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው።
ብዛታቸው ያልታወቀ ጥቁር ዝንጀሮ፣ ጅብ፣ ከርከሮ፣ ድፈርሳ፣ ትልልቅ ጥንቸሎች፣ አረንጓዴ ልባስና ቀይ መንቁር ያላቸው ወፎች፣ የሐበሻ ነብር /Leopard/፣ ከመስከረም እስከ ታኅሳስ ባሉት ወራት ብቻ አኅጉር አቋርጠው የሚመጡ ባለቀለም ወፎችና ለዓይን የሚታክቱ ዓይነታቸውና ብዛታቸው የማይታወቅ ወፎች ደኑን መኖርያ አድረገውት የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰአት በደብረ ማርቆስ ዙሪያ ባለው የደን ቆረጣ የተነሳ እንስሳቱ አንዳንዶችም በሰዎች መኖርያ ቤቶች ውስጥ ዘለው ለመግባት ሲገደዱ ሌሎች ደግሞ ስደትን መርጠዋል።
በአዊ ዞን በገንባሀ ጫካ አካባቢ ሰፍረው የሚገኙ ነዋሪዎች ደግሞ ደኑን አናስቆርጥም በማለት ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ነው።
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈለቀ ተሰማ እየተቆረጡ ያሉ ዛፎች ከመጀመሪያውም ለገበያ ተብለው የተተከሉት እንጅ በተፈጥሮ የበቀሉት አይደሉም ብለዋል።
በደብረማርቆስ አካባቢ የጣውላ ስራ የሚሰራ ፋብሪካ መቋቋሙን የገለጹት አቶ ፈለቀ፣ እየተቆረጠ ያለው ሰው ሰራሽ ደን መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ በክልሉ ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 70/2002 የተቋቋመ ሲሆን፣ ዛፎችን ቆርጦ የመሸጥ እና የማልማት መብት የተሰጠው ተቋም ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ የጉለሌና አራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንዳጋጠማቸው ገለጹ።
ኢሳት ዜና:- የአዲሱ ገበያና የቀጨኔ አካባቢ ነዋሪዎች የውሃ እጥረቱ ለኢኮኖሚና ለጤና ቀውስ እንደዳረጋቸው ተናግረዋል።በዚህ ዓመት በተደጋጋሚ ከአንድ ወር በላይ የቆየ የውሃ እጥረት እንዳጋጠማቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
መንግስት ” የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የቦታ አቀማመጥ ለውሃ ሥርጭቱ አመቺ አለመሆን፣ በእነዚህ ክፍለ ከተሞች ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ፣ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ምክንያት የውሃ መስመሮች መሰበርና መቆረጥ እንዲሁም በውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች አካባቢ ተደጋጋሚ የመብራት ኃይል መቋረጥ” ለውሃ እጥረት መፈጠር ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጿል።
ነዋሪዎቹ ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ውሃን በፈረቃ የሚያገኙበት መንገድ መመቻቸቱን አንድ የመንግስት ባለስልጣን ተናግረዋል።፡
ማእከላዊ አፍሪካን ሪፑብሊክን በማሸነፍ የኢትዮጵያን ታሪክ እንደምንቀይረው አልጠራጠርም ሲል ምንያህል ተሾመ ተናገረ
ኢሳት ዜና:- ምን ያህል ለኢሳት እንደገለጸው በተፈጠረው ነገር በእጅጉ አዝኗል። እኔ በአገሬ ላይ አውቄ እንዲህ አይነት ነገር አልሰራም ያለው ምንያህል፣ ቢጫ ካርድ ከተሰጠው ከ10 ወራት በሁዋላ ብዙ ጨዋታዎችን መጫወቱ ቢጫ ማግኘቱን እንዲዘነጋ እንዳደረገው ገልጿል።
የሚመለከታቸው የስፖርቱ ሀላፊዎች “ሁለት ቢጫ ካርዶችን ማየትክን አልነገሩህም ነበር? ተብሎ ለተጠየቀው ደግሞ አንድ ቢጫ ብቻ እንዳለኝና ከደቡብ አፍሪካ ጋር በማደርገው ጨዋታ እንድጠነቀቅ ተነግሮኝ ነበር፣ ከዚያ ውጭ ግን ማንም ሁለት ቢጫ ካርድ አይተሀልና አትጫወትም ያለኝ የለም በማለት መልሷል።
የደቡብ አፍሪካ የመገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ ላይ 6 ነጥብ እንዲቀነስ የሚያደርጉት ውትወታ የህግ ድጋፍ የሌለው ነው በማለት የሚናገረው ምንያህል፣ ቡድናችን አሁን ባለው አቋሙ ማእከላዊ አፍሪካንም ሆነ ሌላ ጠንካራ ቡድን በማሸነፍ የኢትዮጵያን ታሪክ እንደሚቀይር አምናለሁ ሲል እምነቱን ገልጿል።
ESAT
No comments:
Post a Comment