Tuesday, October 15, 2013

ዋልያው ንሥሩን ጋለበው

click here for pdf
‹ይህቺ ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር የሚጠብቅና የሚታደግ አንዳች ኃይል አለ› የሚባለውን ነገር እንድናምን የሚያደርጉ ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ሕዝቧ ብትን፣ ቅዝቅዝ፣ ድብዝዝ ሲል ከየት እንደሚመጣ ሳይታወቅ ብቅ የሚል፣ እንደ አውሎ አጥለቅልቋት፣ እንደ እቶን አንድዷት፣ እንደ ሐረግ አስተሣስሯት፣ እንደ ደመና ከልሏት፣ እንደ አደይ አበባ አስውቧት፤ እንደ ቀስተ ደመና ቃል ኪዳኗን አድሶ፣ እንደ ጠል አረስርሶ፣ እንደ ሸማ ፍቅር አላብሶ፣ እንደ ደመራ የሀገር ፍቀር ስሜት ለኩሶ፣ እንደ ጨረቃ አድምቆ፣ እንደ ፀሐይ አሙቆ፣ እንደ ሰም አጣብቆ፣ የሚጎበኝ መንፈስ አላት፡፡ እውን ኳስ ነው ያስለቀሰን? እውን ግብ ነው የናፈቀን? እውን የጨዋታ ጥበብ ነው የጠማን? እውን ለዓለም ዋንጫ መድረሳችን ነው እንዲያ ፍቅርን እንደ ሸማ ያላበሰን? እኔ ግን ያየሁት ከዚህ ሁሉ በላይ የሆነውን ነው፡፡ አንዳች ያጣነው ነገር፣ አንዳች የጠማን ነገር፣ አንዳች የተነጠቅነው ነገር፣ አንዳች ቁጭት ውስጥ የከተተን ነገር፣ አንዳች እንደ ዋልታ የሚይዘን፣ እንደ ማገር የሚያስተሣስረን፣ እንደ ተራዳ የሚደግፈን፣ እንደ ደመራ የሚሰበስበን፣ እንደ ችቦ አንድ የሚያደርገን፣ አንዳች ነገር የጠማን ይመስለኛል፡፡

 

ትናንት የኳስ ደጋፊዎችን አልነበረም ያየሁት፣ የኢትዮጵያን ደጋፊዎች እንጂ፡፡ አንድነቷን፣ ኅብሯን፣ ልዕልናዋን፣ ታላቅነቷን የሚደግፉ፤ መለያየትን፣ መከፋፈልን፣ መገፋፋትን፣ መጠፋፋትን፣ የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያንን ነው ያየሁት፡፡ ሰንደቋን ከንሥር በላይ ከፍ ያደረጉት፣ መዝሙሯን በባዶ ሆዳቸው ሰማይ እስኪገረም ድረስ የዘመሩት፣ ከተማዋን በአረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ያጥለቀለቁት ለኳሱ ብቻ አይመስለኝም፡፡ ዓላማቸው ከኳስ በላይ ነበር፡፡ ፍላጎታቸው የኳስ ቡድኑ ሦስት ነጥብ እንዲያመጣ ብቻ አልነበረም፡፡ ፍላጎታቸው አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ሕዝባዊነት፣ ጀግንነት፣ ኢትዮጵያዊነት ሦስት ነጥብ እንዲያመጣ ነበር - አምጣቷልም፡፡ ትናንት ናይጄርያ ቡድናችንን፣ እኛ ታሪካችንን አሸንፈናል፡፡
 

የሰሜኑ ዋልያ ከወጣበት የዳሽን ተራራ ይልቅ፣ ዋልያዎቹ የወጡበት የኢትዮጵያዊነት ተራራ ይበልጥ ነበር፡፡ ከዋልያው ብርቅዬነት የዋልያዎቹ ብርቅዬነት በልጧል፤ እንዲህ አንድ አድርጎ የሚያስደስተን፣ አንድ አድርጎ የሚያስለብሰን፣ አንድ አድርጎ በቁጭት የሚያስለቅሰን አጥተን ነበር፡፡ ልቅሷችን የበደል፣ ደስታችን የግላዊ ጥቅም፣ መሰባሰቢያችን ብሔረሰብ፣ መገናኛችን የወንዝ ቋንቋ፣ መነጋገሪያችን አካባቢያዊ ጉዳይ፣ ንግግራችን ጨቋኝና ተጨቋኝ ሆኖብን ነበር፡፡ ዋልያዎች ሆይ ክብር ይስጣችሁና ከዚያ ከፍ አድርጋችሁናል፡፡ አልተሸነፋችሁም አሸንፋችኋል፡፡ መለያየትን፣ መከፋፈልን፣ መገፋፋትን፣ ወንዝ ለወንዝ መሄድን፣ በሰፋ ግብ አሸንፋችኋል፡፡ ባንዲራ አስለብሳችሁ፣ ለባንዲራ አስዘምራችሁ፣ ለባንዲራ አስለቅሳችሁናል፡፡ልጆቻችን አንድ፣ ከፍ ያለ፣ አድማስ ላይ ብቻ የሚታይ፣ ከሁላችንም ድምር በላይ የሆነ ሀገራዊ ስሜት እንዲሰማቸው አድርጋችኋል፡፡ በየተወሰነ ዘመን ራሱን 

እንደሚያድሰው የከራድዮን ወፍ የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ እንደገና አደሳችሁት፡፡ በየትኛው ሕግና መመሪያ፣ በየትኛው አሠራርና ቅጣት፣ በየትኛው መዋቅርና አደረጃጀት ይህንን የሰንደቅ ዓላማ ፍቅርና ክብር፣ ይህን የሀገር ፍቅርና ክብር፣ ይህን የአንድነት ስሜትና መንፈስ ልናመጣው እንችል ነበር? እንኳን ኖራችሁ፡፡ እናንተ አላዘዛችሁንም፣ ግን አደረግነው፤ አልነገራችሁንም፣ ግን ፈጸምነው፤ ዐዋጅ አላወጣችሁም፣ ግን ተገበርነው፤ መዋቅር አልዘረጋችሁም፣ ግን ልባችን ውስጥ ገባችሁ፤ አልቀጣችሁም፣ ግን ታዘዝናችሁ፤ ጥሪ አላስተላለፋችሁም፣ ግን ሆ ብለን ወጣን፤ አልመዘገባችሁንም፣ ግን አባላችሁ ሆንን፤ ደወል አልደወላችሁም፣ ግን ሌሊት በስታድዮም ሰዓታት አደርን፤ አበል አልከፈላችሁንም፣ ግን ሳይደክመን ተሰለፍን፤ ወደ ከፍታው መራችሁን፣ እኛም በደስታ ተከተልናችሁ፡፡
 

በኳስ ሜዳማ ብራዚልም ይሸነፋል፤ ስፔንም ይሸነፋል፤ የኳስ ወላጅ እናቱ እንግሊዝም ትሸነፋለች፡፡ የአኩስምና የላሊበላ፣ የጀጎልና የጎንደር ግንብ ጥበብ የተሞላበት ያንን የመሰለ ኳስ፣ የጠጅ አጣጣላችን፣ የጠላ አጠማመቃችን፣ የቅመም አቀማመማችን፣ የወጥ አሠራራችን፣ የክትፎና የቆጮ፣ የገንፎና የአምባሻ ጥበባችን በእናንተ ጨዋታ ታየ፡፡ ኳስን ገረማት፡፡ እንግሊዝ አፍ ያዘች፣ ስፔንን ገረማት፣ ብራዚል ልትቀሩ ነው ብላ ቅር አላት፣ ፈረንሳይ አጀብ አለች፣ ጀርመን ተደነቀች፤ ጣልያን ተደመመች፡፡አሁን ስለ እናንተ ስንናገር በኩራት ነው፤ አሁን ልጆቻችን የሚጨዋወቱት በቁጭት ነው፡፡ ‹ዋልያው ንሥሩን ጋልቦታል› እንላለን፡፡ ይህንን ድሮ በ ‹ዜና እስክንድር› ብቻ ነበር የምንሰማው፡፡ እስክንድር ጠቢቡ ወደ ገነት ለመሄድ ብሎ ንሥሩን ከፈረስ ጋር አዳቅሎ ጋለበው አሉ፡፡ እናንተም እንዲሁ ንሥሩን ጋልባችሁ ወደ ልዕልናው ገነት፣ ወደ ኢትዮጵያዊነት ገነት፣ ወደ አንድነት ኤደን ወሰዳችሁን፡፡ ይህቺን ቀን እንደ አድዋ ድል፣ እንደ ዶጋሊ ድል፣ እንደ ሚያዝያ ሃያ ሰባት፣ ስናከብራት ትኖራለች፡፡ የድል ቀን ናትና፡፡ አንድነት መለያየትን፣ ኅብረ ብሔርነት ጠባብነትን፣ ኢትዮጵያዊነት ጎጠኛነትን፣ ሉዓላዊነት ተዋራጅነትን ድል ያደረጉበት ቀን ናት፡፡
by ዳንኤል ክብረት

No comments:

Post a Comment