Sunday, December 8, 2013

በመዲናዋ ምስጢራዊ የወሲብ ገበያ ደርቷል

addis-ababa-new የትላልቅ ድርጅቶች ፀሃፊዎች፣ ሞዴሎችና ተዋናዮች አሉበት
ድንግልናን በ10ሺ ብር የሚያሻሽጡ ደላሎች ሞልተዋል
የከተማዋ ቱባ ባለሃብቶች “የአገልግሎቱ” ተጠቃሚዎች ናቸው

ሲኤምሲ ሣሚት ማዞሪያ አካባቢ ካሉት ዘመናዊ ቪላ ቤቶች በአንደኛው 12ሺ ብር ወርሃዊ ኪራይ እየከፈለች ትኖራለች፡፡ የምታሽከረክረው ኤክስኪዩቲቭ ቶዮታ፣ በየዕለቱ የምትቀያይራቸው እጅግ ውድ ዋጋ ያላቸው አልባሳቶቿና በየመዝናኛ ሥፍራው የምትመዘው ረብጣ ብር የተንደላቀቀ ኑሮ እንደምትመራ ይመሰክራሉ፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናትና መዲናችን አለማቀፋዊ ስብሰባዎችን በምናስተናግድበት ጊዜያት እሷን ፈልጐ ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡
ቦሌ ፍሬንድሽፕ ሕንፃ ላይ በከፈተችው ቡቲክ የምታገኘው ገቢ ይሄን ያህል ሊያዝናናት እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ገቢ ወጪዋን አጥብቃ የማትቆጣጠርበትን ይህንኑ ቡቲኳን ታናሽ እህቷ ትውልበታለች፡፡ እሷም አልፎ አልፎ “ሥራ” በማይኖራት ጊዜ ብቅ እያለች ትጐበኘዋለች፡፡ ታናሽ እህቷ ቤተሰቡን ሁሉ ቀጥ አድርጋ የምታስተዳድረው እህቷ፤ ስለምትሰራው ምስጢራዊ ሥራ አንዳችም የምታውቀው ነገር ያለ አይመስልም፡፡ እሷ የምታውቀው ከተለያዩ የውጪ አገር ሰዎች ጋር የአየር ባየር ንግድ እንደምታጧጡፍና በየጊዜው ወደተለያዩ አገራት ለሥራ ጉዳይ እንደምትመላለስ ብቻ ነው። ሥራዋ የግል ሚስጢሯ ብቻ ሆኖ እንዲኖር የምትፈልገው ህሊና (ስሟ ለዚህ ጽሑፍ የተቀየረ) ይህንን የእህቷን እምነት አጥብቃ ትፈልገዋለች። በተለያዩ የመዝናኛ ሥፍራዎች ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ደንበኞቿ ጋር እየከረመች በመጣች ቁጥር ለእህቷ የተለያዩ ቸኮሌቶችና ስጦታዎችን እየያዘችላት መምጣቷ የእህቷን እምነት አጠናክሮላታል፡፡ እሷ “ቢዝነስ” ብላ የገባችበት ህይወት ገቢ፣ እህቷ ቀኑን ሙሉ ተገትራ ከምትውልበት ቡቲክ ገቢ ጋር ሊወዳደር እንደማይችል ስለሚገባት “ሥራውን” አጥብቃ መያዙን ትፈልገዋለች፡፡ የንግድ ፍቃድ እድሣት፣ ቫት ምዝገባ፣ ሪሲት ማሽን፣ ቀረጥና ታክስ የሚሉ ዝባዝንኬዎች የሌሉበት፣ “ራስን እያስደሰቱ ሌሎችን በማዝናናት” በቀን የሚገኝ ረብጣ ብር ከቡቲኳ ወርሃዊ ገቢ በእጅጉ ይልቃል። ተፈጥሮ ያደላትን ውበትና ማራኪ ቁመናዋን ለገበያ እያቀረቡ በተሻለ ገንዘብ ለመሸጥና ጠቀም ያለ የኮሚሽን ገንዘብ ለመቀበል አሰፍስፈው የሚጠባበቁ ደላላ ደንበኞች አሏት፡፡ ለዚህ ተግባር ብቻ የምትጠቀምበት የሞባይል ስልኳ ሲጮህ “ሥራ” እንደተገኘ እርግጠኛ ትሆናለች። ቅያሬ ልብሶችን የምትይዘበትና ሁሌም ለጉዞ ዝግጁ የምታደርገውን ቦርሣዋን አንጠልጥላ ውልቅ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሥራ የምትንቀሳቀሰው በደላሎቹ መኪና ነው። ደላላው እሷን ካለችበት ወስዶ ወደምትፈለግበት፣ ሥራዋን ስትጨርስ ደግሞ ወደነበረችበት የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ የኮሚሽን ክፍያው እነዚህን አገልግሎቶች ያካተተ ነው፡፡ ህሊና ይህንን ህይወት ላለፉት አራት አመታት ኖራበታለች። ከዚህ ህይወት ስለመውጣትና ቢዝነሱን ስለመተው ለአፍታም አስባ አታውቅም፡፡


ባላት ትርፍ ሰዓት ሁሉ ራሷን እጅግ አድርጋ መጠበቅ፣ ጂም መሥራት፣ ሳውና፣ ስቲምና ማሣጅ በየጊዜው መግባት ታዘወትራለች፡፡ ውበቷንና ጥሩ ቁመናዋን ጠብቃ ለማቆየት ማድረግ የሚገባትን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አትልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለዚህ ሁሉ አዱኛ ያበቃት እሱ በመሆኑ የሚፈልገውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበት ታምናለች፡፡ ይህ የህሊና ህይወት የብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶች ህይወት እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ በመዲናችን አዲስ አበባ እየተጧጧፈ የመጣውን ምስጢራዊ የወሲብ ገበያ የተቀላቀሉ የከተማችን ወጣት ሴቶች የትላልቅ ድርጅቶች ኤክስኪዩቲቭ ፀሐፊዎች፣ የሽያጭ ሰራተኞች፣ ሞዴሎች፣ የፊልም ተዋናዮች፣ የዩኒቨርስቲዎችና የኮሌጅ ተማሪዎችና ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያላጠናቀቁ የሀብታም ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህን ወጣት ሴቶች ለወሲብ ሽያጭ “ሥራ” የሚያመቻቹና የማገናኘት ተግባሩን በቅልጥፍና የሚወጡ ፈረንጆች “ፒምፕ” የሚሏቸው አይነት ደላሎች በከተማችን እየተበራከቱ ነው፡፡ ደላሎቹ ራሳቸው በኔትዎርክ የተሣሰሩ፣ የራሳቸውን መኪና ይዘው የሚንቀሳቀሱ፣ በከተማው ውስጥ አሉ የተባሉ ሆቴል ቤቶችን፣ እንግዳ ማረፊያዎችን፣ መቃሚያ ቤቶችንና የመዝናኛ ሥፍራዎችን በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉ ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment