Monday, November 18, 2013

ሰላማዊ ታጋይን ማሸማቀቅ አይቻልም

በ1997 ዓ.ም የምርጫ ሰሞን ገዢው ፓርቲ በርካሽ ዋጋ ርካሽ ተግባር እንዲፈጽሙ የላካቸው ግለሰቦች የቅንጅትን አመራሮች የሚበዙት በዕድሜ አንጋፋና በትምህርት አንቱታን ያገኙ የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ዳኞችና ሃኪሞች ናቸው፡፡ በዋጋ የተገዙት ግለሰቦች ግን ለማህበራዊ ህይወት ቦታ የሚሰጡ ባለመሆናቸው አመራሮቹን ለጆሮ በሚሰቀጥጥ ስድብ ይሰድቧቸው ነበር፡፡ዶክተር ሃይሉን፣ኢንጂነር ሃይሉ ሻውልን ‹‹አንተ››እያሉ በመደዴ ቃላት ይወርፏቸው ነበር፡፡


ቅንጅቶች ማረሚያ ቤት እንደገቡም ሊያርሟቸው ያስገቧቸው ሰዎች ‹‹ባልታረሙ ቃላት›› ወርፈዋቸዋል፡፡እንዲህ የሚደረገው ሆን ተብሎና ታስቦበት ነው፡፡ኢህአዴግ ለሰላማዊ ትግል ባዳ በመሆኑ በዚህ መንገድ ለመጡ ተቃዋሚዎች ምን አይነት ምላሽ መስጠት እንደሚገባው ስለማያውቅ የራሱን የበላይነት ለማሳየት ሲል ዱርዬ ያፈራል፡፡ፍንዳታ ሌባ ሲመለከት በቅናት ቅጥል ብሎ በፓርላማ ‹‹ፍንዳታ ፖሊስ ››ስለማዘጋጀቱ ይናገራል፡፡በፍንዳታው ሌባና በፍንዳታው ፖሊስ መካከል ግን ያለው ልዩነት ምን እንደሆነ ሊነግረን አይችልም፡፡ ሌብነት ወንጀል የሚሆነው እጅ ከፍንጅ ሌባው ሲያዝ ነው የሚል ሰው የስርዓቱ ቁንጮ ሲሆንና በህዝብ ግብር በሚተዳደር ቴሌቪዥን ‹‹እጅ እቆርጣለሁ ››በማለት ዜጋውን የሚያስፈራራ መሪ ምን አይነት ደህንነት፣ፖሊስና የስለላ ማዕከል ሊኖረው እንደሚችል መገመት ህመም ነው፡፡

እነዚህ ከማህበራዊ ህይወት እንዲያፈነግጡ ተደርገው በዋጋ የተገዙ ሰዎች በሞሉበት አገር ሰላማዊ ታጋዩች የሚከፍሉት መስዋዕትነት ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑትን መምህር አበበ አካሉን ተመልከቱ፡፡መምህሩ ወደ ትምህርት ቤት እያመሩ የመንግስት ታርጋ በለጠፈ ላንድ ክሩዘር የመጡና ደህንነት ነን ባሉ ሶስት ሰዎች ሰወር ወዳለቦታ ተወስደው ድብደባ ደርሶባቸው በተቃውሞ ፖለቲካ የሚቀጥሉ ከሆነ በቤተሰቦቻቸው ጭምር አደጋ እንደሚያደርሱባቸው በመንገር ጥለዋቸው ሄደዋል፡፡

ስርዓቱ ፖሊስ፣ፍርድ ቤት፣መሳሪያ፣የስለላ መረብና ወህኒ ቤቶች ያሉት ቢሆንም መምህሩን ህጋዊ ሽፋን ያላቸውን ተቋማት በመጠቀም ሊያስመስልባቸው እንኳን አልፈለገም፡፡ከዚህ ይልቅ የውንብድና ስራ ለመስራት በመምረጥ አበበን አጥቅቷቸዋል፡፡መምህሩ ለሚዲያ በሰጡት አስተያየት ‹‹ለቤተሰቦቼ እንኳን ልነግራቸው የማልችላቸውን አሳፋሪና አስነዋሪ በደል ፈጽመውብኛል››ብለዋል፡፡አበበ ላይ የተፈጸመው ምን ይሆን በማለት ድርጊቱን ለማወቅ መጨነቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡

የተፈጸመው ድርጊት የቱንም ያህል የከፋና አስነዋሪ ቢሆን አስነዋሪና ከኢትዩጵያዊ ጨዋነት የሚጣረሰው ቀድሞውኑ ይህንን ለሚያውቁና በዚህ ውስጥ ላለፉ ነው፡፡ በድርጊቱ የአቤንም ሆነ የየትኛውንም ሰላማዊ ታገይ መንፈስ መስበርና ማሸማቀቅ አለመቻሉም በትግሉ ተስፋ እንዳንቆርጥ ያደርገናል፡፡አቤ ላይ የተደረገው ነገር አስነዋሪነቱ የሚታየው በእርሱ ላይ ሳይሆን በአድራጊቹ ስብዕና ነው፡፡ያልተነገረው ድርጊታቸው ብዙ ሺህዎችን ከተኙበት በመቀስቀስ በትግሉ እንዲገፉ ከማድረግ ባሻገር የዚያኛውን ካምፕ መደዴነት፣ዋልጌነትና ስድ አደግነት ወለል አድርጎ ያሳያል፡፡
Dawit Solomon

No comments:

Post a Comment