Monday, October 14, 2013

የትናንቱን የአዲስ አበባ የፈንጂ ፍንዳታ ያደረሱት ሁለት ሶማሊያውያን አሸባሪዎች መሆናቸውን ፖሊስ ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2006 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት በአዲስ አበባ  ቦሌ  ክፍለ ከተማ  የደረሰው የፈንጂ ፍንዳታ በሁለት ሶማሊያውያን  አሸባሪዎች የተፈፀመ መሆኑን የኢትዮጵያ  ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ ።
የኢትዮጵያ  ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አሰፋ አብዩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስረዱት ፥ በክፍለ  ከተማው ወረዳ 01 ቀበሌ 01 በተለምዶ ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ  በአንድ የመኖሪያ ቤት  ውስጥ ነው ፍንዳታው የደረሰው ።
ፖሊስ ፍንዳታው ፈንጂ መሆኑንና ፥  በጥቅም ላይ የዋለው ቲ ኤም ቲ የተባለ  የፈንጂ ዓይነት መሆኑን እንደደረሰበት  ገልፀዋል ።
ፍንዳታውንም  ሁለት  ሶማሊያውያን ማቀነባበራቸውን ፖሊስ እንዳረጋገጠና  ግለሰቦቹ የአሸባሪ ቡድኑ አልሸባብ አባል መሆናቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንዳሉም ነው ጀነራል አሰፋ አብዩ ያስረዱት ።
ከሁለቱ  አሸባሪዎች መካከል አንደኛው ወገቡ ላይ የታጠቀና ለአጥፍቶ ጠፊ ተግባር የተዘጋጀ መሆኑን  የሚያሳይ ነው ።

ሌላኛው  አሸባሪ በሻንጣ ፈንጂ  የያዘ ሲሆን ፥ የፈነዳውም ፈንጂ በሻንጣው ውስጥ የነበረ መሆኑን ነው ጀነራል አሰፋ ያስረዱት ።
ለአጥፍቶ  ጠፊ ተግባር  ሲዘጋጅ የነበረው ግለሰብ የታጠቀው ፈንጂ  ግን  እንዳልፈነዳ አመልክተዋል ።
አሸባሪዎቹ በአጠቃላይ  ሶስት ፈንጂዎችንም ይዘው ነበር ።

አሸባሪዎቹ ህዝብ ባለበት ስፍራ አደጋ ለማድረስ ተከራይተው በነበሩበት ቤት ውስጥ ሲዘጋጁ ፍንዳታው ደርሷል ብሎ ፖሊስ እንደሚጠረጥር ነው የጠቆሙት ።
ከአሸባሪዎቹ  ጋር ፖሊስ የእጅ ቦምቦችንና ሽጉጥ ከነጥይቱ  አግኝቷል ።

ከዚህ የምንማረው  
ጀነራል አሰፋ አብዩ እንደሚሉት ሶማሊያውያን አሸባሪዎቹ  ቤቱን ከተከራዩ ከ22  እስከ 23 ቀን ይሆናቸዋል ።
እስከ  ስድስት የሚደርሱ  ቤቶችን በከተማዋ  የሚያከራዩት የቤቱ ባለቤቶች  ስለነዚህ  ግለሰቦች ስምን ጨምሮ  ማንነታቸውን  እንደማያውቁ ነው የተደረሰበት ።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ቤቱንም ሆነ  መኪናውን ሲያከራይ ስለተከራዩ ማንነት በቂ  እውቀት ይዞ ፥  መታወቂያና ፓስፖርት ተመልክቶ  መሆን  እንዳለበት ነው ያሳሰቡት ።
የሚያገኛቸውን መረጃዎች በአቅራቢያው ለሚገኝ የፖሊስ  ተቋም  መስጠት  ግዴታው መሆኑን በመረዳትም ፥  ሽብርተኝነተን ከፖሊስ ጎን  ሆኖ  እንዲከላከል ጥሪ አቀርበዋል ።
ተያያዥ ዜና

በአዲስ አበባ የፈንጂ ፍንዳታ ደረሰ



No comments:

Post a Comment