የኢትዮጲያ እግር ኳስ: በስሜትና በእዉነት መካከል!

“ከታሪክ መማር የማይፈልግ ሰዉ ታሪካዊ ስህተትን ለመድገም የተረገመ ነዉ”
በሰኢድ ኪያር
እንደመግቢያ…
አሁን ሰማይ የተሰቀሉ ስሜቶች ቀዝቅዘዋል፤በጭፍን ዋልያዉን ከማሞገስና ከመስቀል በእዉነታዎች ላይ መወያየት ተጀምርዋል፤በመጀመሪያዉ ጎን ደግሞ ናይጄሪያን በመልስ ጨዋታ ስለማሸነፍ መዘመሩን ቀጥልዋል፤ይህ ሚድያዉን ያጠቃለለ ፉከራ ከጥቅምት 3ቱ በጥቂት ግን ወሳኝ ነገር ለየት ይላል፤ቢያንስ ቢያንስ ”እንዴት???” የሚለዉን ቀም ነገር ማካተት ጀምረዋል፤ይህ ጽሁፍም ያልተስተዋለዉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ስሜት ዝብርቅርቅ ይዳስሳል..ከእዉነት ይልቅ ስሜትን ስለተከተሉት ወቅቶች………
የዛን ቀን ደስታ ልዩ ነበር፤ከዳሪሰላም ታንዛኒያ ሲቃ የተሞላባቸዉ ድምጾች የኢትዮጲያን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ አበሰሩ፤ለእግር ኳሱ ትንሳኤ ቀን እንደሆነም በመነገሩ አዲስ አበባ እና መላ ኢትዮጲያም ተነቃንቀዋል፤በለንደን ኦሎምፒክ ወንዶቹ ሲያቅታቸዉ እንስቶቹ ግን የተለመደዉን ወርቅ አምጥተዉ ህዝቡን አኩርተዋል፤እናም በእግር ኳሱ የዉጤት ማማ ሴቶች ነገሱበት፤”የሴቶች እግር ኳሱ መነቀቃት”ም በይፋ ተነገረ!!በየመንገዱ ሉሲ– በየራድዮ ጣቢያዉ- ጋዜጦች እና የቲቪ መስኮቶች የሉሲ ገድል ዝማሬ ጣሪያዉን ነካ፤ሉሲዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸዉ ይበል የሚያሰኝ ነገር ነዉ፤እንዴት አለፉ የሚለዉ ግን በሞራልና በጮቤ ረገጣዉ መሀል ተሸሽገዉ ቦታ አላገኙም፤ሁሉም ቀርቶ ሉሲዎቹ ከዚህ በፊት ለአፍሪካ ዋንጫ ባለፉባቸዉ ዉድድሮች እንኩዋን ምን ገጠማቸዉ የሚለዉን ማየት አልተቻለም፤አላማችን ለአለም ዋንጫ ማለፍ ነዉ—ስሜት የነገሰበት የሁሉም የርእይ ስንቅ ነበር፤ ዉድድሩ ሲጀመር ግን ይህ ሁላ የስሜት ሰቀላ ዉሀ ተቸለሰበት፤ከመጀመሪያዉ ደቂቃ አንስቶ ኮትዲቫሮች ግብ ማምረት ጀመሩ፤5-0 ጨዋታዉ አለቀ፤እዚህ ላይ ቡድኑ ልምድ የለዉም እንዳይባል 3ተኛ የአፍሪካ ዋንጫቸዉን የሚጫወቱ–ለ2ተኛ ጊዜ ሉሲን በአህጉሪቱ መድረክ የሚወክሉ…በተለያዩ ማጣሪያዎች ልምድ ያላቸዉ ተጫዋቾች የተሰባሰቡበት ቡድን ነዉ፤ግን አልቻለም፤ያቃተዉ ደግሞ የኮትዲቫሮችን ማጥቃት ማቆም ብቻ አይደለም መሀል ሜዳዉን አልፎ መሄድ የዳገት ያህል ለሉሲዎቹ ከበደ፤ናይጄሪያ ቀጣዩን ጨዋታ 3-0 ረታች፤ከካሜሩን ጋር 0-0 የሉሲዎቹ መጨረሻ ከ8ቱ ቡድኖች 8ተኛ ..ብዙ ግቦች ያስተናገዱ ግን አስደንጋጭ ሙከራ እንኳን ያላደረጉ ሁነዉ ተሸኙ፤ከምንም በላይ ‘’ተነቃቃ’’ የተባለዉ እግር ኳስ አሸለበ፤የያኔዉ አይነት ጎሮ ሸባዮ አሁን በሉሲዎቹ አከባቢ የለም፤አርቴፊሻሉ መነቃቃት በክለቦች የዋንጫ ጨዋታ እንኳን አይኖችን መግዛት አልቻለም፤”ብዙ ትምህርት አግኝተንበታል “–የተለመደዉ ሽንፈት ሰራሽ መልስ ተከተለ፤ ይህ ከሆነ 1 ድፍን አመት ሁኖታል፤ስለ ሉሲ ያኔ የተዘመረዉን ያህል አሁን ስለ ሉሲ የሚያወራም የለም፤እንደእምቧይ ካብ በሚናዱ የስሜት ዝብርቅርቆች መሀል ከተገኙት የኢትዮ ቡድኖች አንዱ ሆኑ ..ሉሲዎች ዋልያ…. ከኢትዮጲያና ሱዳን ጨዋታ በፊት–ግዮን ሆቴል –“የኢትዮጲያ እግር ኳስ እንዴት ከወደቀበት እናንሳ?’’ በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ቀረበ፤ፌዴሬሽኑ ነዉ የጥናት ባለቤቱ..እናም ከትምህርት ተቋማት የተዉጣጡ ዶክተሮችም ሳይቀሩ ተሳትፈዉበታል፤ማጠቃለያዉ –የኢትዮጲያ ኳስ እንዲያድግ መሰራት የሚገባቸዉ ነገሮች ተብለዉ…. –አደረጃጀትን ዘመናዊ ማድረግ —-ፕሮጀክት በስፋት እንዲኖሩ –ወጥ ስልጠና ማንዋል ማዘጋጀት —አካል ብቃት ላይ በሚገባ መስራት..ወዘተ…. በሚል ጥናቱ አስቀመጠ፤ለዚህም ተሰብሳቢዉ ማረጋገጫ ቃሉን ሰጥቶ ተለያየ፤ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት ቢያንስ ቢያንስ አመታት ይፈጃሉ፤አጥኚዎቹም ሆኑ ተሳታፊዎቹ ይህንን ነገር አላምጠዉ ሣይጨርሱ ዋልያዉ ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈ፤እዚህ ላይ ሁነኛ መነጋገሪያዎች መነሳት ይገባቸዉ ነበር፤ወይ ጥናቱ ፉርሽ ነዉ!! አልያም ጥናቱ ትክከል ሆኖ ቡድኑ በአጋጣሚ አለፈ፤ካልሆነም ደግሞ ጥናቱ እንደችግር ያስቀመጣቸዉ ሀሳቦች እንዳሉ ሆነዉ ጠንካራ ለአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፍ ቡድን ሊሰራ ይችላል….!!.ስሜት መር የሆነዉ እግር ኳሱ ግን ጆሮ ዳባ ብሎ ጉዞዉን ቀጠለ! ቤኒን ጋር አቻ..ሱዳንም ጋር አቻ ወጥቶ ዋልያዉ ደቡብ አፍሪካ ደረሰ፤ይህ በርግጥም ከታሪክ አንጻር ትልቅ አጋጣሚ ነዉ፤ግን ከስሜት ምህዋር ያልወጣ ያለጊዜዉ የደረሰ አልያም የማይደገም ስለመሆኑ ማሳያዉ በዉድድሩ ላይ የታየዉ ቡድን ነበር፤”ዋንጫ እንደርሳለን—ባይሆን እንኳን 4ቱ ዉስጥ ከገባን በቂያችን ነዉ!!”የሚል እቅድም ተነድፎ ነበር፤ ከዛምቢያ ጋር አቻ የወጣዉ ቡድን ሜዳ ላይ ባሉ መነጻጸሪያዎች ሁሉ(ካርድንም ሳይጨምር) ተበልጥዋል፤በስሜት በሚነጉደዉ እይታ ግን ይህ ቡድን የአፍሪካ ባርሴሎና ተባለ፤ቀጠለና በቡርኪና ፋሶ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ እናም 4ት ግቦች አስተናገደ፤በስሜት የተወጠሩት ልቦች አሁን ተንፈስ አሉ፤ናይጄሪያም ብልጫዉን ወስዶ 2-0 አሸነፈ፤ከተሳታፊ ቡድኖች በአነስተኛ ነጥብ በአነስተኛ ሙከራ እናም በብዙ ግቦች በማስተናገድ ግምባር ቀደም ሁኖም ተመለሰ፤”እንደጀማሪ የነጻ ትግል ተፋላሚ”!!! ይህ ነገር በዚህ ትዉልድ ብቻ የተከሰተ አይደለም፤እግር ኳሱ— ከዚህ በፊት የነበሩት ቡድኖች አንዴ ብልጭ ካዛም ድርግም በሚሉ ዉጤቶች ተጭበርብሮ በግድ የኢትዮጲያን እግር ኳስ ትንሳኤ መስክሯል
አዘናጊዎቹ ድሎች
3ተኛዉ የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጲያ ትልቁ ታሪክ ነዉ፤ሉቻኖ ቫሳሎ ከንጉሱ እጅ ታሪካዊዉን የአፍሪካ ዋንጫ ከተቀበለ ወዲህ ማንም ኢትዮጲያዊ ያንን መድገም አልቻለም፤ይሔ ድል ለያኔዉ ትዉልድ ብቻ ሳይሆን” ኳስ ድሮ ቀረ” ለሚለዉ መካካለኛዉ የእግር ኳስ ዘመን ሰዎችም እንደማሳያ ይቆጠራል፤የያኔዉ ድል እንዴት ተገኘ?የሚለዉን ዋነኛ ነገር ያልመረመረዉ ትዉልድ ለተከታታይ ዉድቀቶቹ ምክንያት እስኪያጣ ድረስ ግራ ተጋብትዋል፤አስኪ ዋንጫ የበላ ቡድን እንዲህ አይነት የሽንፈት ጉዞ ሲከተለዉ ምን ይባላል፤—ዉጤት ያመጣበትን ምክንያት አለማወቁ ከማለት ዉጭ!!!ተከታዩ ዉጤት ታሪካዊዉ ድል አድራጊ የኢትዮጲያ ቡድን የአፍሪካን ዋንጫ ካነሳ በሁዋላ ባሉት አመታት ያስመዘገባቸዉ ዉጤቶች ናቸዉ!! ከ4ተኛዉ እስከ 13ተኛዉ የሊቢያ አፍሪካ ዋንጫ 6ት ዉድድሮችን ተካፍሎ..ካደረጋቸዉ 19 ጨዋታዎች 14ቱን በሽንፈት 1ዱን አቻ 4ቱን በማሸነፍ አጠናቅዋል፤41 ግቦች አስተናግዶዋል 20 ብቻ አስቖጠወርዋል..21 እዳ ማለት ነዉ ሲወራረድ፤ያስከበረዉ የበላይነት አልያም ያስጠበቀዉ ክብርም አልነበረም፤ጭራሽኑ ከ13ተኛዉ በሁዋላ 31 አመታት እልም ብሎ ጠፍትዋል፤መነቃቃትን ፈጥሮ የነበረዉ ቡድን የተከተለዉ ታሪክ እንግዲህ ይህ ነዉ!!!! ነገርየዉ ይቀጥላል፤የሲካፋ ዋንጫ በኢትዮጲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ ኢትዮጵያ ዋንጫ አነሳች..ጎሮ ወሸባዉ ቀልጦ በቀጣይ ሽንፈቶች ደግሞ እንደበረዶ መቅለጥ ተከትለዋል፤የክለቦችም ወግ ቢሆን ከዚህ እላፊ አልሄደም፤ አለም ዋንጫ… “ አርጀንቲና አትሄዱም”….. “አርጀንቲና አትሄዱም”…. የሚሉ የተስፋ መቁረጥ ድምጾች በአዲስ አበባ ስታድየም የተሰሙት በጋርዚያቶ ተመርቶ ለአለም ዋንጫ ባለፈዉ የወጣት ቡድን ላይ ነበር፤በህዝብ እና በካፍ ቀና እርዳታ ወደ አለም ዋንጫዉ ማለፉን ያረጋገጠዉ ወጣት ቡድን በጥሎ ማለፋ በአንጎላ 5-2 በደረጃ ጨዋታ በግብጽ 2-0 በጨዋታ ብልጫ ጭምር ሲሸነፍ ህዝቡ ወደ አለም ዋንጫ የማለፍ ትርጉም አልባ መሆኑን በማሰብ ነዉ.አርጀንቲና አትሄዱም ያለዉ!! አሁን ከ13 አመታት በሁዋላ የያኔዉን ለአለም ዋንጫ ያለፈ ቡድን ስናየዉ በርግጥም ተመልካቹ ትክክል እንደነበር ማረጋገጥ እንችላለን፤ቡድኑ እንደምንም ማጣሪያዉን አልፎ(ከ5ጨዋታ 1ዱን በልዩ ህግ አሸንፎ) በአለም ዋንጫዉ በታናናሾቹ 3ቱንም ጨዋታ ተሸንፎ ተመለሰ፤(ከ8 አንድ አሸንፎ ማለት ነዉ)!ወጣት የተባሉቱ በዋናዉ ቡድን ይህንን መድገም አልቻሉም፤ጭራሽም ለረጅም አመታት ለመጫወት የበቁት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸዉ፤ እዚህ ላይ ዋናዉ ነገር ተጫዋቾቹ ያገኙትን ድል ማንኳሰስ አይደለም፤ለሁሉም ኢትዮጲያን በአለም ዋንጫ ለወከሉ..ማጣሪያዉን ለተጫወቱ..ላሰለጠኑ ላገዙ—ለሁሉም ትልቅ ክብርና ምስጋና ሊቸር ይገባል፤ዋናዉ ቁም ነገር ግን የያኔዉ ድክመት ለዛሬዉ ማስተማሪያ ስለሚሆን ዋነኛ ድክቶቹን ነቅሶ ማዉጣት ነዉ፤እናም ኢትዮጲያ ዛሬ ላይ ሁና የዛሬ 13 አመት ለአለም ዋንጫ ያለፈዉ ቡድንዋ ምን እንደጠቀማት መናገር አለመቻልዋ ነዉ! አለም ዋንጫን ማለፍ ሁነኛ ጥቅም ከሌለዉ የወራት ሆይ ሆይ ሆይታ እናም ቀጥሎ ሀዘን የሚያስከትል ከሆነ ዋጋ ቢስነቱ ያይላል!!በተደጋጋሚ የመሳተፍ የሚያስችል ቁመና ያለዉ ጠንካራ ቡድን ከሆነ በሴካፋ ዉድድርም ቢሆን ጥንካሬዉ ሲገነባ ለነገ ተስፋ ይሠጣል፤
፤
የአሁኑ ዋልያ…
የላይኛዎቹ መነሻዎች አሁን ካለዉ ቡድን ጋር ለማያያዝ ጠቃሚ ይሆናሉ፤የዋልያዉ የአፍሪካ ዋንጫ ሂደት ሲገመገም ከማለፍ በስተቀር በዉድድሩ ላይ ያሳየዉ ነገር ጠንካራ እንዳልሆነ ምስክር አያስፈልገዉም፤ከዛ በሁዋላ ባደረጋቸዉ የአለም ዋንጫ ጨዋታዎችም ቦትስዋናን እና ሴንትራል አፍሪካን በደርሶ መልስ ደቡብ አፍሪካን አዲስ አበባ ላይ ማሸነፍ ቢችልም ጨዋታዎቹ ለቡድኑ ጥንካሬ ምስክር መሆን አልቻሉም፤አዲስ አበባም ላይ ሆኑ ዉጭ የተደረጉቱ ጨዋታዎች አስጨናቂ ነበሩ፤የጨዋታዎቹ ፍጻሜ ፊሽካ እስኪነፋ ድረስ ደረትን ነፍቶ የቡድኑ ጠንካራ ነገር ይህ ነዉ ለማለት አዳጋች ነበር፤የተጋጣሚዎች መቅለል–ማለትም እንደከዚህ ቀደሞቹ ቡድኖች አይነት የነ ግብጽ-ካሜሮን–ቱኒዚያ አይነት ጠንካራ ቡድኖች ጋር አለመጫወቱ–እንዲሁም በዉጤት ደረጃ ጥሩ ባይሆንም በማሸነፍ እድለኛነት እዚህ ደርስዋል ቀደም ብለን እንዳየናቸዉ ቡድኖች አንዴ ታይቶ ብን ብሎ የሚጠፋ ክስተት እንዳይሆን አሁን ላይ ያሉትን ህጸጾች ነቅሶ ማዉጣት ግድ ይላል፤ዋልያዉ የዛሬ 2ት አመት ከተሳተፈበት ሴካፋ ጀምሮ ተጋጣሚን እንዴት እንደሚቀርብ ለማወቅ ከባድ ነዉ፤በአብዛኛዉ ከአሰልጣኞቹ እንደሚሰማዉም..ተጋጣሚ ከተከላከለ የሚያጠቃ— ካጠቃ ደግሞ የሚከላከል ስለመሆኑ ነዉ፤ይህ ነገር ማሸነፍን እንዴት እንደሚመጣ አልያም ሽንፈት በምን ምክንያት እንደመጣ የሚያስተምር አይደለም፤ቄሱም መጽሀፉም ዝም ብሎ ከመቀጠል ዉጭ! የአሁኑ ዋልያ አጨዋወት ግምት ላይ የተመሰረተ ረጅም ኳሶችን አዘዉታሪ መሆኑ በጨዋታዎች ላይ ተመልክተናል፤ይህ ደግሞ አሁን አለም እየተቀየረበት ካለዉ አጨዋወት በሚልየን ምይሎች ርቀት ላይ ያስቀምጠዋል፤ተከላካዮች ኳስን ተጫዉቶ ከመዉጣት ይልቅ በረጅሙ ጠልዞ እንደገና የመጠቂያ ምንጭ እንደሆኑ በተደጋጋሚ አይተናል፤አማካዩ ክፍል ለፈጠራ ዝግ ነዉ፤አለም ትቶት የወጣዉን በተከላካይ አማካዮችን አብዝቶ ያለጨዋታ አቀጣጣይ አነስተኛ ፈጠራ ያላቸዉን ተጫዋቾች መጠቀም የአሁኑን ዋልያ መሀል ሜዳ እጅጉን ደካማ ያደርገዋል፤3ት ቅብብል ለማድረግ የሚቸገር አማካይ ክፍል በንጽጽር ጥሩ ለሚባሉት አጥቂዎች የሚያበረክተዉ አስተዋጽኦ ኢምንት ነዉ፤በዚህ ቦታ በተደጋጋሚ የአሰልጣኞች ምርጫ ያልነበረዉ ሽመልስ በቀለ ለብቻዉ ኢትዮጲያ ምን አይነት ተጫዋቾች እንደሚያስፈልጋት የሚያሳይ ሁኑዋል፤ እነዚህና እና መሰረታዊ የሚባሉ የቡድን ዉህደት ችግር ያለበት ዋልያ ከምንም በላይ አቆለጳጵሶ፤ከአቅሙ በላይ አወድሶ፤የህዝብን ስሜት አንሮ በስተመጨረሻ አሸማቃቂ አይነት ብልጫ ሲመጣ ምክንያት መደርደር ብልህነት አይሆንም፤ብዙዎች ዋልያዉ ነገ ከሚያደርገዉ ጨዋታ በፊት የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጉ እንደሚጎዳዉ ይናገራሉ፤ነገር ግን ዋልያዉ እስካሁን ካሸነፈባቸዉ ጨዋታዎች ምንም አይነት ድክመት ለማሻሻል ሳይችል ሌላ ጨዋታ ማድረግ ትርጉም አልባነቱ ይጎላል፤ አርቆ ማሰብ በዋልያዉ አከባቢ መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ነዉ፤ናይጄሪያን ማሸነፍ ይቻላል፤አለም ላይ ያለን ጠንካራ ቡድንንም እንዲሁ…ነገር ግን ምንም ጥንካሬ ሳይኖር ትልቁን ሆነ ትንሹን ቡድን ማሸነፍ ዋጋቢስ ነዉ፤ከዚህ በፊት የነበሩት ድንገቴ ቡድኖች እንዳመጡት የሚረሳ ዉጤት ከመመስከር በስተቀር!!
ናይጄሪያ…የኋላን ማስተዋል….
ስለ ናይጄሪያ ጨዋታ ሲነሳ ሰዎች የኋላን ማየት አስፈላጊ አለመሆኑን ሲናገሩ ነበር፤ምክንያቱም ናይጄሪያ ምን ያህል በሽንፈት እንዳቆሰለን ስለሚታወቅ…ነገሩ ግን ህልም ተፈርቶ….እንደሚባለዉ ነዉ፤ናይጄሪያ በልጦ እስከዛሬ አሸንፎናል፤ይህ ሀቅ ነዉ..ዛሬም ቢወራ ከታሪክነት ባለፈ ለምን እንደበለጠን መማሪያ ይሆናል፤ትላንት የበለጠበትን መንገድ የያኔ ተጫዋቾች (አሁን በአሰልጣኝነት እና ዙሪያዉ ያሉ) በሚገባ አስረድተዉ አሁን ዋልያዉ እንዴት መብለጥና ማሸነፍ እንዳለብን ማስረዳት ይችላሉ፤አለበለዚያ ግን የኋላን ትቶ አልያም ማንሳቱን ፈርቶ የአሁኑን ብቻ ማሰብ ጎዶሎነት ይሆናል፤ጸሀፊዉ ዳንኤል ክብረት እንዳስቀመጠዉ…. ’’ከታሪክ መማር የማይፈልግ ሰዉ ታሪካዊ ስህተትን ለመድገም የተረገመ ነዉ፤እንዲህ የሚያደርግ ግን እንስሳ ብቻ ነዉ፤እንስሳት ታሪክ የላቸዉም፤ታሪክ ስለሌላቸዉ የዛሬ 1ሺ አመት አንድ በሬ የሰራዉን ስህተት የዛሬዉ በሬ ይደግመዋል፤የዛሬ 3 አመት አንድ በግ የሰራዉን ስህተት ዛሬም ያዉ በግ ሊሰራዉ ይችላል፤የዛሬ 600 አመት ምድርን ስትጭር የነበረችዉ ዶሮ ዛሬም እንደምትጭረዉ ማለት ነዉ፤ዶሮዋ ለመጫር ነዉ እንጂ ለመብረር ልታስብ አትችልም፤ሰዉ ግን ከዚህ ዉጭ ነዉ፤ሰዉ ከትላንት ይማራል..ስህተቱን ያርማል……ስለዚህ የሰዉ ልጅ የትላንቱን ጥሩ ይዞ እንዲቀጥልና መጥፎዉን እንዲያርም የጎበጠዉን እንዲያቀና…ተብሎ የታሪክ ትምህርት የሚሰጠዉ..’’
ከስሜት ወደ እዉነት…
ኢትዮጲያ እንድታሸንፍ የማይፈልግ የለም፤አስተማማኝ ቡድን ቢኖራት ምን ግዜም የምትታወቅበት ጥንካሬ ብታሳይ የሁሉም ምኞት ነዉ፤ነገር ግን ነገ በማይደገም አካሄድ ቡድንዋ በዉጤት ሲደለል ዝም ማለትም ተገቢ አይሆንም፤ዉጤት ያመጡ ሰዎች ክብር ይገባቸዋል፤ሽልማትም ቢጎርፍላቸዉ አስፈላጊ እና የሚበረታታ ነዉ፤ነገር ግን ዉጤት ያመጡበትን መንገድ መመርመር ደግሞ እዉቅና ከመስጠት የተለየ እይታን ይጠይቃል፤ጥሩ ያልሆነን ቡድን እላይ ሰቅሎ ሲፈጠፈጥ ከመሳቀቅ ከመነሻዉ እያሸነፈም ቢሆን በድፍረት ስህተቱን መጠቆም አስፈላጊ ነዉ፤ የባለፈዉ ሳምንት ጨዋታንም በዚህ መነጽር መቃኘቱ ጠቃሚ ነዉ፤የመጀመሪያዉ ነገር ከጨዋታዉ በፊት ይነገሩ የነበሩ የሁለቱ በድኖች ልዩነቶች አሁንም እንዳሉ ተረጋግጥዋል፤ናይጄሪያ በኬሺ የተጫዋችነት ዘመን የመንግስቱ ወርቁን ቡድን በአካል ብቃት ጥንካሬ እንደበለጡት ዛሬም የሰዉነትን ቡደን ከ30 አመታት በሁዋላም በልጠዋል፤ይህን ነገር ከእኔ ከጻሀፊዉ..ከናንተ አንባቢዎቸ እና ከአሰልጣኞች በላይ ተጫዋቾቹ ያቁታል፤ሁሌም በተደጋጋሚ ይናገሩታል፤ለዚህም ይመስላል ያለወትሮዉ በግምት ይላኩ የነበሩ ኳሶች የቀነሱት…ተጫዋቾቹ ኳስዋን በሚችሉት መንገድ በመሬት በአጭር ቅብብል ለመብለጥ ጥረዋል፤ከሌላዉ ጊዜ በተለየም ከተከላካዮቹ ደፍሮ የሚቀበል አማካይ ብቅ ብልዋል፤እሱም አዳነ ግርማ ነዉ፤የዋልያዎቹን ልምምድ ላለፉት 2ት አመታት በቅርበት ስከታተል የኳስ ብልጫን ለመዉሰድ የሚያስቸል ልዩ ስልጠና አላየሁም፤እናም አዳነ እና ጓደኞቹ ያደርጉ የነበሩት እንቅስቃሴ በትሬኒንግ የተነደፈ ስላለመሆኑ የቅብብላቸዉ መጨረሻ ያሳብቃል፤ለ6ት በራሳቸዉ ሜዳ ይቀባበላሉ..ከዛም በግምት ኳሶች ይጣሉና አጥቂዎቹ አላስፈላጊ ድካም ዉስጥ ይገባሉ፤ያም ቢሆን ግን ናይጄሪያን በፈለገዉ መጠን እንዳይንቀሳቀስ አድርገዋል፤የዚህ ነገር መነሻ የሆነዉ ተጫዋች በጊዜ ከተቀየረ ደግሞ ከርሞም ይህ አይነቱ አጨዋወት ተፈላጊ አለመሆኑን ያሳያል፤አሰልጣኝ ሰዉነት ከጨዋተዉ በሁዋላ ከአንድ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ..”አሁን ጊዜዉ የመጫወት ነዉ፤ተጫዉቶ ማሸነፍ ያስፈልጋል፤ይህንንም ለመተግበር ሞክረናል” የሚል አንደምታ ያለዉ አስተያየት ሰጥተዋል ፤የመጀመሪያዉ ነገር መጫወት ከተፈለገ..እናም በመጫወት ብልጫ መዉስድ እንደሚቻል ከተረጋገጠ መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾችን ለምን አልተካተቱም ?ይሆናል ጥያቄዉ…….ለማስረጃ ያህል መሀል ክፍሉን ለ90 ደቂቃ ተፈራርቀዉ ከተጫወቱት አስራት..አዳነ..አዲስ..እና ምንያህል ..ዉስጥ አንዳቸዉም በክለባቸዉ የጨዋታ አቀጣጣይነት ሚና ኑርዋቸዉ አያቅም፤አዳነ አጥቂ..አስራት እና አዲስ ቀሚ..ምንያህል የክንፍ ተጫዋቾች ናቸዉ፤እናም የመሀል ክፍል ብልጫ ያለመሀል ተጫዋች..ለዚያዉም የመፍጠር ብቃቱ ደካማ የሆነን ይዞ ማሰብ ከባድ ይሆናል፤ሀገሪቱ ደግሞ የአማካይ ተጫዋች ደሀ አይደለችም..ሌላዉን እንተወዉና የአዲስ አበባ ስታድየም መጫወቻ ሜዳ ሁሌም የመሀል ክፍሉ ሳር በቶሎ መበላት ለዚህ የማይናገር ምስክር ነዉ!!! ናይጄሪያ ጋር እንዴት መጫወት እንዳለብ እና እንዴት መጫወት እንደሌለብን በጨዋታዉ ታይትዋል፤የዚህ ቀን ችግር ግን የተጀመረዉ ዋልያዉ አሸናፊ ሆኖ ከማንም በላይ በተባለባቸዉ የቦትስዋና..ሴንትራል አፍሪካ..ደቡብ አፍሪካ ጨዋታዎችም ጭምርም ነበር፤በነዚህ ጨዋታዎች በየደቂቃዉ የሚጠልዝ..ኳስ ከእግሬ ዉጭልኝ በሚል መንፈስ የሚጫወት ቡድን ነበር፤ያም ቢሆን ግን ስላሸነፈ ከነስህተቱ ተንቆለጳጰሰ፤ድል ማድረግ እናም መመስገን በጣሙን ጥሩ ነገር ነዉ፤ነገር ግን ምንም ላይ ያልተመሰረተ ድል ነገ ምንም ላይ ሲጥል የናይጄሪያ አይነት ዱብ እዳ ያስከትላል፤
መፍትሄ…
ችግር የመፍትሄ ቁልፍ ነዉ፤እናም ኢትዮጵያ እግር ኳሴ አድግዋል ባለችበትም ሆነ በደከመችበት ጊዜ ያለመታከት የሚያሸነፍኑን የምእራብና ሰሜን አፍሪካ ቡድኖችን ለመብለጥ ወደ እዉነታዉ መምጣት አለብን፤”እኔ ጢቅ ጢቅ ጨዋታ የሚጫወት አልፈልግም.የሚጋጭ የሚፋለጥ እንጂ” የሚል አስተሳብ ያለዉ አሰልጣኝ ናይጄሪያም ሲመጣ ተጋጥቶና ተፋልጦ አሸንፎ ማሳየት ይኖርበታል፤አልያም ደግሞ አስቀድሞ በኳስ መብለጥ አለብን የሚለዉን መያዥ ይኖርበታል፤እኔ ይህንን የምጽፈዉ ላለፈዉ ቡድን አይደለም፤ከዚህ በኋላ ለሚመጣዉ ነዉ፤እንኳን አሰልጣኙና ባለሙያዉ ቀርቶ ተመልካቹ እንኳን ለይቶ ኳስ የሚጫወቱ የዉጭ ቡድኖችን የነፍሱ ያህል በሚወድበት ሀገር ለጥለዛ ና አካል ግዝፈት የሚሰጠዉ ትኩረት መቅረት አለበት፤እከሌ ምን ያህል ኳሶችን አጨናገፈ ሳይሆና እከሌ ምን ያህል ኳሶችን አስተካክሎ ሠጠ መመዘኛ መሆን አለበት፤፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ክህሎት ያልዋቸዉ ተጫዋቾች ሀገር መሆንዋ ለክርክር ማቅረብ ጉንጭ ማልፋት ነዉ፤አለምም በዚህ በዉብ እግር ኳስ ቅኝት እየተመራ መሆኑ ለእግር ኳሱ ትልቅ እድል ነዉ፤አለም ተጫዉቶ ስለማሸነፍ እያዜመ ነዉ፤ጀርመን ከጉልበት ወደ ጥበብ መንገዱን ጠርግዋል፤ስፔን እግር ኳሱን በአጭር ቅብብል መደብ አናቱ ላይ ከወጣች ቆይታለች፤ዋልያዉስ???አፍሪካን ለመቆጣጠር ጊዜዉ አሁን ነዉ!!ከፍለጠዉ ቁረጠዉ አጨዋወት ወደ ጭንቅላት ጨዋታ መቀየር..ለዚህ ደሞ በቂ ተጫዋቾች በኢትዮጲያ ይገኛሉ፤እናም ለዋልያዉ ትንሳኤ በመልሱ የካላባር ጨዋታ ሆነ በቀጣየቹ ዉድድሮች ይህንን መሞከሩ በእዉር ድንብር ከመሄድ በእዉቀት አለምን መከተልን ያስገኝለታል!!!!
No comments:
Post a Comment