አንዲት ተረት፤ ባለ በቅሎው ሰውዬ!

ባለበቅሎው ሰውዬ በጠዋት ወጣ፤ ከልጁም ጋር ነበር፡፡ በበቅሎዋ ላይ እርሱ ተፈናጦ ልጁ ደግሞ ሉጓሟን እየሰባ ሲሄዱ ሲሄዱ ሲሄዱ… እመንገዳቸው ላይ ሰዎች አጋጠሟቸው፡፡ ሰዎቹም ክፉኛ ተቹት፡፡
እንደምን ያለው ራስ ወዳድ ነው ባካችሁ ልጁን ልጓም እያስጎተተ እርሱ በቅሎዋን ይጋልባል፡፡ አሉት፡፡
ይሄን ጊዜ ሰውየው ደንገጥ አለ፡፡ እውነትም ምን ነካኝ ሲል ዩልኝታ ያዘው፡፡ ከዛ… በቅሎዋ ላይ ልጁን ጭኖ ራሱ መጎተት ጀመረ፡፡ ከዛ ሲሄዱ ሲሄዱ… መንገድ ላይ ሰዎች አገኟቸው፡፡ አሉትም፡፡
አንተዬ እንደምን ያለከው ከንቱ ነህ… ልጅህን በበቅሎ ጭነህ አንተ የምትጎትተው ልጁ ሰው ማክበር ከወዲሁ እንዳይማር …መረን አንዲወጣ ልታደርገው ነውን…! አሉት፡፡
ባለቅሎውም፤ አረ… እውነትም ምን ነካኝ አለ … በል ውረድ ሲልም ልጁን አዘዘወው በቅሎይቱንም ሌጣ አድርገው ሁለቱም በእግር መሄድ ጀመሩ፡፡ ሲሄዱ ሲሄዱ ሲሄዱ… መንገድ ላይ ሰው አጋጠማቸው፡፡
ወ…ይ ጉድ የዛሬው ባለበቅሎ ደግሞ እንደምን ያለው ዘመናይ ነው… ሌጣ በቅሎ ይዞ ልጁም ራሱም በእግሩ የሚሄድ… ብለው አሽሟጠጡት፡፡
ወ…ይ ጣጣ… ባለበቅሎው ግራ ገባው… እስቲ የቀረችቱን አንድ እድል ልሞክር ብሎ ራሱም ልጁም በቅሎቱን ተፈናጠው… መጭ አሏት፡፡ በቅሎዋ እያቃሰተች እነርሱም ተጣበው ሲሄዱ ሲሄዱ ሲሄዱ… ሰዎች መንገድ ላይ አጋጠሟቸው፡፡
እንዲህም አላሏቸወው፤ እስቲ እንደው ምንም የማታውቅ የእግዜር እንስሳ አፍ የላትም፣ አቤት አትልም ብለህ ነው እንዲ ለሁለት የተሳፈራችሁባት…! ብለው ኮነኑት፡፡
ይሄንን ሁሉ የተመለከተች አንዲት ጦጣ (ያው ተረት ላይ ጦጣ አትጠፋም ብዬ እንጂ ጦጣ እንኳ እንዲህ አላለችም፡፡)
ብቻ ጦጢት ሆዬ እንዲህ አለች አሉ፤
አንተ ባለበቅሎ ሰውዬ ሰዎች አስተያየት በሰጡህ ቁጥር አቀማመጥ እና አካሄድህን ቀየርህ አትችለውም፡፡ ስለዚህ አንተ ትክክል ነው ያልከውን አድርግ፡፡ ከሰዎች ትችት ይልቅ የህሊናህን ቁጣ ፍራ…! ማንም ለመጉዳት ሆን ብለህ እና አስበህ እንዲሁም በክፉ ልቦና ተነሳስተህ፣ ብሎም ለግል ጥቅምህ ስትል በሌሎች ላይ መጥፎ ከማድረግ ተቆጠብ ከዛ መንገዱ ጨርቅ ይሆንልሃል…! አለችው ይባላል፡፡ (አይ ጦጣ… ተረት ላይ እኮ ምሁር ናት!)
ተረቴን መልሱ ፌስቡኬን በላይክ አብሱ!!!
No comments:
Post a Comment