የታፈሱት ሰልፈኞች ሁሉ የታጎሩት በአራዳ ፖሊስ መምሪያ ጊቢ ውስጥ ነበር፡፡ ጊቢው ውስጥ እንደደረስኩ ከፊት ለፊቴ ደረጃው ላይ የተኮለኮሉትን ሰልፈኞች ተመለከትኩ፡፡ ወጣቶቹ ታፍሰው የገቡ ሳይሆን ወደው የተሰበሰቡ ይመስሉ ነበር፡፡ እንዲያውም በገባሁ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ጮክ ብለው ይዘፍኑ ጀመር፡-
‹‹… ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም፣ ባባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም…››

ጊቢው ውስጥ ከሌሎቹ እንዳልቀላቀልና ብቻዬን እንድቆይ አድርገውኛል፡፡ ባንድ በኩል ስልኬ ላይ ያሉትን ፎቶዎች አጥፍተው ይፈቱኛል፣ ጉዞዬም ይቀጥላል በሚል ደስ ብሎኛል፡፡ በሌላ በኩል በዓይን የማውቃቸውን እነዚያን ልጆች ቀረብ ብዬ አለማነጋገሬ ቆጭቶኛል፡፡ በዚህ መሐል ግን ሁሉም እየሄዱ ቃል ሲሰጡ ቆዩ (ቃል ሲባል ቃል እንዳይመስላችሁ፤ ከስም አንስቶ የኔ የምትሉትን ነገር በሙሉ ይጠይቋችኋል)፤ ከዚያም የኔም ተራ ደረሰና ቃል ሰጥቼ ሳበቃ እኔም በቀላሉ እንደማልሰናበት ሲያረዱኝ የጓዝ ኮተቴን ሁሉ አስመዝግቤ እዚያው ተጠቃለልኩ፡፡
ከዚያም ቃል የመስጠቱ ሥነ ስርዓት ቀጠለ፤ የመጣው ሁሉ በራሱ መንገድ ያንኑ ጥያቄ መልሶ፣ መላልሶ እያንዳንዱን ታሳሪ (ተጠርጣሪ ልበል ይሆን?) ይጠይቃል፤ እያንዳንዱም ተጠርጣሪ ይመልሳል፡፡ ሆኖም ብዙዎቹን መርማሪዎች የብስጭት መንስኤ የሚሆን ነገር ባለራዕዮቹ ወጣቶች ሳይናገሩ አይወጡም ነበር፡፡ ብሔር ሲባሉ ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ይላሉ፡፡ ይህንን የሚሉት ‹‹ብሔር›› የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹አገር›› መሆኑን እያጣቀሱ ነው፡፡ ታዲያ ይህ አባባል ለመርማሪዎቹ የሚያበሳጭ ድፍረት ነበር፡፡
ፖሊሶቹ የሆነችውን ሁሉ እየደወሉ፣ ለአለቆቻቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ መሐል ከሰልፈኞቹ አንዱ ለብሶት የነበረው ባንዲራ ላይ በእስክርቢቶ የጻፈውን ደብዳቤ ከስልኩ ወዲያ ላለ ሰው በንባብ ሲያጽፉት ሰምቻለሁ፡፡ ጽሑፉ ባብዛኛው መንፈሳዊ ነው ቢባል ይቀላል፡፡ ‹‹ለእመቤታችን በአስራትነት የተሰጠችው አገራችን ኢትዮጵያ…›› ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡http://www.blogger.com/blogger.g?blogID=3499323826983623926#editor
ምርመራው/ጥያቄው ቀጥሏል፤ ከጠያቂዎቹ መካከል የደኅንነት እና የኢንሳ ሰዎችም ነበሩበት፡፡ ከጥያቄዎቻቸውም ውስጥ የኢሜይል አድራሻ እና የይለፍ ቃል፣ የፌስቡክ አድራሻ እና የይለፍ ቃልም ይጠይቁ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ታሳሪ (ተጠርጣሪ አልልም) ስሙን በቪድዮ ካሜራ ፊት እንዲናገር ይገደድ ነበር፡፡ እንግዲህ ይህንኛው መጀመሪያ ላይ እያንዳንዱ ሰው ከተነሳው ፎቶ በተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ የጅምላ እስር ውስጥ ካስተዋልኳቸው ጉዳዮች ውስጥ የሴቶቻችንን ጀግንነት ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ እኔ ያለምንም ማንገራገር ምስሌን አስቀርጬ ወደቃለመጠይቁ ሳልፍ የሰማያዊ ፓርቲዋ አመራር አባል ሐና ዋለልኝ ‹‹አልቀረጽም፣ አሻፈረኝ›› ብላ ስትሟገት ድምፅዋ ይሰማኝ ነበር፡፡
ሲመሽ ይፈቱን ይሆን? እዚሁ ያሳድሩን ይሆን? ሌላ ቦታ ይወስዱን ይሆን? ምን ብለው ይከሱን ይሆን? እየተባባልን የተሰባሰብንባት አንዲት በረንዳ መሳይ ክፍል ውስጥ፣ ኢቴቪ በቀጥታ የሚያስተላልፋቸውን የአዳማ እና የመቐለ የኦሕዴድ እና የሕወሓት ስብሰባዎች መኮምኮም ጀመርን፡፡ አሳሪዎቻችንም በስልክ አለቆቻቸውን እያነጋገሩ ሽር ጉዳቸውን አጧጡፈውታል፡፡ ኢቴቪም ብቻውን በዓሉን ማክበር አልቻለም፡፡ መብራቱ ብልጭ ድርግም አበዛ፡፡ ብልጭ ድርግም አልኩ እንጂ ያበዛውስ ድርግም ማለት ነው፤ አልፎ፣ አልፎ ግን ላፍታ ብልጭ እያለ ነበር፡፡ በጨለማው ውስጥ ራታችንን በጨለማ ተቋደስን፡፡ ሁላችንም ምሳ ያልበላን ቢሆንም አንዳንዶች ግን ቁርሳቸውንም አልበሉም፡፡
የመታሰራችን ዜና በማኅበራዊ አውታሮች በመጠኑ ቢስተገባም የብዙዎቻችን ቤተሰቦች ግን አልሰሙም፤ ደውሎ የማሳወቅ ዕድሉም አልተሰጠንም፡፡ እዚያው ጨለማ ውስጥ ከቆየን በኋላ ወደ 3፡00 ሰዓት ገደማ ወደ ጃንሜዳ አካባቢ የሚገኝ ማረሚያ (እስር ቤት) በሁለት ዙር ተወሰድን ከ30 በላይ እስረኞች አንድ ላስቲክ ብቻ ወለሉ ላይ የተነጠፈበት ክፍል ውስጥ ብንታጎርም በእርስ በርሳችን ጫወታ ተጠምደን ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ እኛ ወደዚህ እስር ቤት ስንዛወር ቀይ ለባሽዋ ዓለም ተለቅቃ ወደቤቷ ሄዳለች፡፡) የሄድንበት በሰልፉ ዋዜማ ሲቀሰቅሱ ከታሰሩ ሌሎች ጋር ተቀላቅለናል፡፡ የጅምላ እስሩ ጉዳይ በዋዜማው እንደተጀመረ ያወቅኩትም ያኔ ነው፡፡ ቀድመው ከታሰሩት ውስጥ ሁለቱ ክፉኛ ቡጢ እና ካልቾ ቀምሰው እንደሆነ ለማወቅ እስኪናገሩ መጠበቅ አያስፈልገንም ነበር፤ የአንደኛው ጃኬት የደረቀ ደም ከፊትለፊት ይታይበታል፡፡
ለአምስት ሰዓት ዐሥራ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን እንደገና እንድንንቀሳቀስ ተነገረን፡፡ ከኛ ቀደም ብለው ሴቶቹም ወደቀጨኔ (ችሎት መድኃኔዓለም ኮንዴሚኒዬም አጠገበ ያለ) ወረዳ 9 ማረሚያ ቤት እንደተወሰዱ እና ከኛም ውስጥ 12ቶቻችን መከተል እንዳለብን ተነገረን፡፡ እዚያ እንደደረስን ግን ምነው እዚያው በቀረን የሚያስብል ትዕይንት ገጠመን፡፡ እያንዳንዱ ክፍል እላይ በላይ ተደራርበው በተኙ እስረኞች ተጨናንቋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጫማ ማስቀመጫ ቦታ እንኳን በክፍሉ ውስጥ ስለሌለ ጫማዎቻችንን ውጪ እያስቀመጥን እንድንገባ ተገደድን፡፡ ሦስቱ (አራት ሜትር በአራት ሜትር የሚገመቱ) ክፍሎች ውስጥ አንዱ 37፣ አንዱ 34 እና ሌላኛው ውስጥ 30 እስረኞችን ይዟል፡፡
እንዳጋጣሚ 30 ሰዎች የያዘው ውስጥ ነበር እኔ የደረሰኝ፡፡ የኛ ክፍል ይሻላል ተብሎ ዶ/ር ያዕቆብንም አመጧቸው፡፡ ጉዳዩ በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ እኛስ ባልደከመ ጉልበታችን እንችለዋለን፤ ለርሳቸው ግን በጣም ፈታኝ እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው፡፡ ክፍሉ በጣም ጥቅጥቅ ብሎ ከመሞላቱ የተነሳ ለኛ ቦታ ለማግኘት የቤቱ ካቦ ተነስቶ እያንዳንዱን እስረኛ እየቀሰቀሰ ማጠጋጋት ነበረበት፡፡ በቦታ ጥበት ምክንያት ደረቁ ወለል ላይ በአንድ ጎናችን እንድንተኛ ከመገደዳችን የተነሳ እኔ ይህን ጽሑፍ እስከምጽፍበት ሰዓት ድረስ ቁርቋሬው የፈጠረው ሕመም ጎኔን አያስነካኝም፡፡ ካቦው አጠጋግቶልን ሲጨርስ ሁላችንንም የገቢ ገንዘብ ተቀበለን እና ተኛን፡፡ እዚያ ክፍል ውስጥ መተኛት ማለት፣ መተኛት ማለት አይደለም፡፡ የክፍሉ መታፈን እና አስቀያሚ ጠረን፣ ሙቀት፣ በዚያ ላይ እየተቀባበሉ የሚያጨሱት ሲጃራ ጢስ፣ ከዚያ እና ከዚህ የሚተኮስ የፈስ ሽታ… ብቻ የአበሳ ናሙና ነበር፡፡ ሌሊቱን ሲዘንብ ማደሩ ግን በከፊልም ቢሆን የክፍሉን አየር አቀዝቅዞታል፤ ችግሩ ዝናቡ ውጪ ያስቀመጥነው ጫማ ውስጥ ውኃ መሙላቱ ብቻ ነበር፡፡
እንደምንም ነጋልንና ወደፍርድ ቤት እንደምንሄድ ተነግሮን ጥንድ ጥንድ እየተደረግ በካቴና ተቆላለፍን፡፡ ከመሐከላችን አንዱ የማኅበሩ አባል፣ ፀጉሩን አጎፍሮ ስለነበር (ለፍርድ ቤቱ ውበት አይመጥንም ብለው ይሆናል) ይቆረጥ አሉና መቀስ አንስተው ይከመክሙት ጀመር፡፡ ፀጉሩን ቆርጠው ሲጨርሱ አሰለፉንና ካቴናችንን ፈቱት፡፡ ‹‹ፍርድ ቤት መወሰዳችሁ ቀርቷል፣ ምናልባት ፖሊስ ጉዳዩን ይፈታዋል›› ተባልንና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወደጃንሜዳ ማረሚያ ቤት መልሰው ወሰዱን፡፡ እዚያ ስንደርስ ለፖሊስ ዋስ እያቀረብን እንድንፈታ ተፈቀደልን፡፡ ቀድሞውንም የታሰርነው ያለወንጀል በመሆኑ አስገራሚ ውለታ አልነበረም፡፡
የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የሚያስፈልገው ቅድመ ሁኔታ ለመስተዳድሩ ማሳወቅ ሲሆን፣ መስተዳድሩ ደግሞ በ24 ሰዓት ውስጥ ‹‹አይሆንም›› የሚል ደብዳቤ ካልጻፈ እንደተፈቀደ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ሰልፍ ማድረጉ ሕጋዊ ስህተት የለበትም፣ ጉዳዩ ባንድ ጀምበር የተወለደ ሳይሆን ጋዜጦች ዜና የሰሩለት፣ ቁጥቦቹ ሬድዮዎች ሳይቀሩ ያወሩለት ጉዳይ ስለሆነ ወንጀል ነው ፍርድ ቤት ሊያቀርቡት አይችሉም/አይገባቸውምም፡፡ ነገር ግን ‹‹…ካፈርኩ አይመልሰኝ…›› ይመስላል በዋስትና እንድንፈታ ፈቅደው ያገቱብንን ንብረቶቻችንን እየመለሱ መጋቢት 9/2005 እኩለ ቀን ላይ አሰናበቱን፡፡
No comments:
Post a Comment