Friday, September 28, 2012

የጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሣለኝ ልዩ ቃለ-ምልልስ ከቪኦኤ ጋር

አቶ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መንበረ መራሂ መንግሥቱን ከተረከቡ ወዲህ ለውጭ መገናኛ ብዙኃን አካል ቃለምልልስ ሲሰጡ ይህ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ የሰጡት ልዩ ቃለ-ምልልስ የመጀመሪያቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሃገር ውስጥ ጉዳዮቿ፣ በውጭ ፖሊሲዋና እንቅስቃሴዎቿ ላይ ያነጋገራቸው የቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት ኃላፊ ፒተር ኃይንላይን ለአቶ ኃይለማርያም ካቀረባቸው ጥያቄዎች አንዱ ኢሕአዴግ የሕወሓት ተፅዕኖ እንዳለበት ይነገራል - የሚል ነበር፡፡

አቶ ኃይለማርያም ለጥያቄው መልስ መስጠት የጀመሩት የኢሕአዴግን የተፈጥሮ ሂደት በመተንተን ሲሆን የጥምረቱ አባል የሆኑት አራቱ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ - ሕወሓት፣ ብሔረ-አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ - ብአዴን፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት - ኦሕዴድ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ - ደኢሕዴን እንደአፈጣጠራቸውና በትግሉ ውስጥ እንዳሣለፉት ጊዜ ጥንካሬያቸው፣ አቅምና ልምዳቸው አንዱ ከሌላው እንደሚለይ አመልክተዋል፡፡

“ይሁን እንጂ - አሉ አቶ ኃይለማርያም - ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የተካሄደው የሕዳሴ ሂደት አዲስና የነጠረ የፓርቲውን ፖሊሲ፣ ስትራተጂና አቅጣጫ እንዲወጣ አድርጓል፡፡…” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጠሉና “… በዚህም መሠረት ሁሉም ፓርቲዎች ወደ አንድ ንቅናቄ ገቡና አንድ ዓይነት አቅጣጫን፣ አንድ ዓይነት ልምድና የአሠራር አካሄድ በፓርቲው የውስጥ ሥርዓት አሠፈኑና ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል ሥፍራ ያዙ፡፡ በመሆኑም በሁሉም የኢሕአዴግ መዋቅሮች ውስጥ፤ ለምሣሌ በምክር ቤቱ ውስጥ፣ በፓርቲው ጉባዔ፣ በሁሉም ኃላፊነቶችና የሥራ ምደባዎች ላይ አራቱም ፓርቲዎች እኩል ናቸው፡፡ ለዚህ እማኙ እኔ የዚህ ሂደት ውጤት መሆኔ ነው፡፡ እኔ በሕይወት ያለሁ ማሣያ ነኝ፡፡ 

ኢሕአዴግ በዚህኛው ወይም በዚያኛው ቡድን ተፅዕኖ ምክንያት በተ ወሰኑ ቡድኖች ወይም የጎሣ ቡድኖች ላይ የተዛባ አያያዝ አለው ብለው ለሚገምቱ ይህ የሃሰት እና ተጨባጭነት የሌለው ግምት ነው፡፡ በመሆኑም በፓርቲያችን የውስጥ ሥርዓት ውስጥ የመጀመሪያው ጉዳይ ዴሞክራሲያዊ ግንኙት ነው፡፡ የጥንካሬአችን መሠረት የፓርቲው የውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ከውጭ ሆነው የሚያስቡት፤ የሚያስቡት ፓርቲውን የውስጡን ሳያውቁ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን የፓርቲውን አሠራርና ፓርቲው እንዴት እንደሚሠራ ብዥታ ላለባቸው ሰዎች ማስጨበጥ አለብን፡፡ 

ይህ ፓርቲ በውስጡ ዴሞክራሲያዊ ነው፤ ውሣኔዎቹና ሥራዎቹ የሚከናወኑት በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው፡፡ በመሆኑም ይህኛው ወይም ሌላኛው ፓርቲ ተፅዕኖ ያደርጋል፤ ወይም ይጫናል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አራቱም አባል ፓርቲዎች እኩል ቁጥር ያለው ውክልና አላቸው፡፡ ከፈለጉም በዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚፈልጉት ተፅዕኖ ሁሉ አላቸው፡፡ በመሆኑም ዋናው ጠቃሚ ጉዳይ በፓርቲው ውስጥ ዴሞክራሲ አለ፤ እየሠራ ያለ ነው፡፡ 

በዚህ ምክንያት ሰዎች ያላቸውን ግምት አልቀበልም፡፡ ለማሣያም እኔ የተመረጥኩት በአራቱም ፓርቲዎች ተወካዮች በሙሉ ድምፅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእኔ ፓርቲ በደኢሕዴን ብቻ ሣይሆን በሌሎቹም ጭምር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ባይኖረን ኖሮ ለየፓርቲያችን ወገናዊ ሆነን እንቀር ነበር፡፡ በመሆኑም የእኔ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆኜ መመረጥ ዘግይቶም የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የዚህ ሂደት ማሣያ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ የጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሣለኝ ልዩ ቃለ-ምልልስ ከቪኦኤ ጋር - ክፍል 1::

No comments:

Post a Comment