በአማራ ክልላዊ መንግስት ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የአስተዳደሩ ጽ/ቤት መቃጠሉን የዜና ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡ ምንጮቻችን “ነሐሴ 27/ 2004 ዓ.ም ሌሊት የአስተዳደሩ ጽ/ቤት ተቃጥሎአል” ብለዋል፡፡
ከአካባቢው የዜና ምንጮቻችን ከላኩልን መረጃ መረዳት እንደተቻለው ወረዳው ጽ/ቤት በገጠመው ቃጠሎ የተለያዩ ሰነዶችና ኮምፒውተሮች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን የቃጠሎው መነሻ ምን እንደሆነ በግልጽ አለመታወቁ ጉዳዩን የበለጠ አነጋጋሪ አድርጐታል ፡፡ ምንጮቻችን አያይዘው ሲናገሩ “ቃጠሎው የተፈፀመው የአቶ መለስ ቀብር በተፈፀመበት ዕለት መሆኑ በአካባቢው የበለጠ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል” ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ጽ/ቤታቸው ተቃጠለ የተባለባቸውን የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ አላቸው አየለና የወረዳው የማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብቴ ገድሉ ዘንድ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ስለማይነሳ ሐሳባቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡
No comments:
Post a Comment